የጸጋው ፍሬያማነት
ፍሬያማ በሆነ አገልግሎት ውስጥ የእግዚአብሔር ጸጋ
በኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌዎድ
Light To My Path Book Distribution
Sydney Mines, N.S. CANADA B1V1Y5
የጸጋው ፍሬያማነት
የቅጂ መብት © 2017 በኤፍ. ዋይኑ ማ ሌዎድ
መብት ሁሉ የተጠበቀ ነው፡፡ከጸሐፊው የጽሑፍ ፈቃድ ውጪ፤የትኛውም የዚህ መጽሐፍ አካል በማንኛውም መልክ ወይም መንገድ ሊሰራጭ ወይም ሊተላለፍ አይችልም።
“በዚሀ መጸሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተወሰዱት ከESV® Bible (The Holy Bible, English Standard Version®), copyright © 2001 by Crossway, a publishing ministry of Good News Publishers. ነው፡፡ የተፈቀደ፡፡ መብት ሁሉ የተጠበቀ ነው፡፡”
ልዩ ምስጋና በእርማት ለረዳችኝ፤
ለዲያን ማክ ሎይድ
ማውጫ
መቅድም
ምዕራፍ 1- አሳቹ እና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች
ምዕራፍ 2- ሃገር እና ሕዝብ የሌለው ሰው
ምዕራፍ 3- በቀለኛው ብርቱ ሰው እና የእስራኤል ጠላቶች ሽንፈት
ምዕራፍ 4- በሃገር ላይ ተጽዕኖ ያመጣው ታጋዩ አባት
ምዕራፍ 5- የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚለማመደው እረኛ
ምዕራፍ 6- በነብያት ድካም የሚገለጠው የእግዚኢብሔር ኃይል
ምዕራፍ 7 - የባዕድ ነገስታት እና የእግዚአብሔር ዓላማ
ምዕራፍ 8 - ኢየሱስ የመረጣቸው ሰዎች
ምዕራፍ 9 - ዓለማዊ ስኬት እና ታማኝነት
ምዕራፍ10 - ምስጋናውን መውሰድ
ምዕራፍ11 - ዓለማዊ ስኬት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው መንፈሳዊ ጉዳዩች
ምዕራፍ 12 - በድካም ውስጥ ያለ ፍሬያማነት
ምዕራፍ 13 - የማጠቃለያ ሐሳቦች
በዘመናችን በአገልግሎት የበለጠ ውጤታማ ስለመሆን የሚያስተምሩ ብዙ ስልጠኛዎች እና መጻሕፍት አሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች እና ስልጠናዎች እንዴት የተሻለ ሰባኪ መሆን እንደምትችሉ መመሪያ ይሰጣሉ። አብያተ ክርስቲያናትን እንዴት መትከል እና ማሳደግ እንዳለብን የሚያሳዩ ጉባኤዎች አሉ። እነዚህ ክስተቶች በጣም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። በግሌ እግዚአብሔር እነዚህን አጋጣሚዎች ተጠቅሞ አገልግሎቴን ለመቅረፅ ረድቶኛል። ለአንዳንድ መንፈሳዊ እድገቴ የሚሆኑ ጠቃሚ ነገሮችን ለማግኘት እንደዚህ ዓይነት ስልጠኛዎች ማግኘት አስፈላጊ ነው።
ይህ ዓይነቱ ሥልጠና ጠቃሚ ቢሆንም፣የበለጠ መረዳት የሚያስፈልገን መንፈሳዊ ውጤታማነት እና ፍሬያማነት የተመሠረተው በትምህርታችን ወይም በምንጠቀማቸው ዘዴዎች ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ መሆኑ ነው። ለመንግሥቱ የምንጠቀመው የሰለጠንን ስለሆን ሳይሆን እግዚአብሔር በጸጋው በእኛ ለመጠቀም በመምረጡ ምክንያት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና፤ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር በሚጠቀምባቸው ሰዎች እደነቃለሁ። ምናልባት መደበኛ ሥልጠና ያልነበረውን ሰው እግዚአብሔር በኃይል ሙሉ በሙሉ ሲጠቀምበት ስታዩ በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ዓመታትን በሥልጠና ያሳለፋችሁት ጊዜ ወደ አዕምሯችሁ ይመጣ ይሆናል። ምናልባት በቅድስና እና በቅንነት ለመኖር የተቻላችሁን ሁሉ አድርጋችሁ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ክርስቲያናዊ የሆነ የሕይወት ምስክርነት የሌለውን ሰው ለምን ይጠቀማል ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የሰለጠኑ እና በጥሩ የአኗኗር ዘይቤ የሚመላላሱ ሰዎችን በመጠቀም ብቻ የተወሰነ አይደለም። እሱ ብዙውን ጊዜ አጠያያቂ የሆነ የኋላ ታሪክ እና ታማኝነት ያላቸው ወንዶችን እና ሴቶችን ተጠቅሟል። ፍሬያማነት በእኔ ማንነት ወይም ተሰጥኦ የሚመጣ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ጸጋ ውጤት መሆኑን ወደ መረዳት እየመጣሁ ነው።
የዚህ ጥናት ትኩረት እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸውን ዓይነት ሰዎች መርምሮ ማወቅ ነው። ከትምህርት ወይም መልካም የአኗኗር ዘይቤ አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ የማነሳው ምንም ጥያቄ የለኝም። ሆኖም እኔ ማሳየት የምፈልገው በአገልግሎት ውስጥ የሚመጣ ውጤታማነት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ብቻ ነው። የአገልግሎታችን ስኬት እና ፍሬያማነት የመጣው በመልካም ትምህርታችን፣በክህሎታችን ወይም መልካም አኗኗራችን ምክንያት የመጣ በማድረግ ለእግዚአብሔር ክብርን በመስጠት ፈንታ ምስጋናውን ለራሳችን እንወስድ ይሆን?
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ፣በአገልግሎት ውስጥ የሚመጣ ውጤታማነት ከእኔ ጥረት ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ የተደገፈ መሆኑን እረዳለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ትምህርቴ እና ልምዴ እንቅፋት ስለሆኑብኝ እግዚአብሔርን መታመን እና መፈለግን አልቻልኩም ነበር። ከእኔ ጋር ይህንን ጥናት ስትጀምሩ ለፍሬያማ አገልግሎት የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚስፈልጋችሁ እንደሚያስታውሳችሁ አምናለሁ።
ኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌዎድ
ምዕራፍ 1- አሳቹ እና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል
ይህንን ጥናት ስንጀምር፤ግባችን በወንዶች እና ሴቶች ልጆች በጉድለቶቻቸው እና ድካማቸው ዓላማዎቹን የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ማየት ነው።እግዚአብሔር እንዲጠቀምብን ፍጹም መሆን ስለማያስፈልገን ምን ያህል አመስጋኞች ነን።
ጥናታችንን ያዕቆብ ከተባለው ሰው እንጀምር። ያዕቆብ የታላቁ የአይሁድ አባት የሆነው ይስሐቅ ልጅ ነበር። የይስሐቅ ሚስት ርብቃ ልጅ መውለድ አትችልም ነበር። እግዚአብሔር የይስሐቅን ጸሎት ሰምቶ ማህፀኗን ከፈተላት። (ዘፍጥረት 25:21 ተመልከቱ) ርብቃም ጸነሰች ከዚያም መንታ ልጆችን ያዕቆብንና ወንድሙን ኤሳውን ወለደች።
በዚህ ጸንሰ-ሀሳብ ውስጥ ጉልህ የሆነው ስለ እነዚህ መንትዮች የተነገረው ትንቢት ነበር። በእርግዝናዋ ወቅት ርብቃ የሆነ ችግር እንዳለ ይሰማት ነበር። መንትዮቹ “በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤” (ዘፍጥረት 25፡22) ። ይህ ርብቃን ስላስጨነቃት ጌታን ስለዚህ ጉዳይ ጠየቀች፡
23 እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። ዘፍጥረት 25
እግዚአብሔር ለእነዚህ ሁለት ልጆች ዓላማ ነበረው። የሁለት የተለያየ ሕዝብ አባት ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ዓላማ ግን ታናሹ ከወንድሙ የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን እና ታላቁም ታናሹን እንዲያገለግል ነበር።
የመውለጃው ጊዜ ሲደርስ የበኩር ልጁ ኤሳው ሲባል ታናሹም ያዕቆብ ተብሎ ተጠራ። ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፣ኤሳው ሲወለድ፣ታናሽ ወንድሙ ያዕቆብ ተረከዙን ይዞ ነበር። ወላጆቹ ይህንን ክስተት አስተውለው ድርጊቱን የሚወክል ስም ሰጡት። አዳም ክላርክ ለያዕቆብ ስለተሰጠው ስም እንዲህ ይላል፡
ስሙ ያዕቆብ ብሎ ተጠራ–ያም ከአዕካብ የተወሰደ ነው፤ትርጓሜውም፤ተንኮል፤ማታለል፤ማፈናቀል ወ.ዘ.ተ ማለት ነው፤የአንድን ሰው ተረከዝ በመያዝ መገልበጥ ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ይህ ስም ለያዕቆብ ተሰጠ፤ምክንያቱም የወንድሙን ተረከዝ ይዞ ነበርና፤ያም የወንድሙን ኤሳውን ስፍራ ስለመያዙ እና ብኩርናውን በማታለል ስለመውሰዱ ምሳሌ ነበር፡፡ (Commentary on the Bible by Adam Clarke (CLARKE) Electronic edition copyright © 2015 by Laridian, Inc., Marion Iowa. All rights reserved. “Commentary on the Bible by Adam Clarke.” Marion, IA: Laridian, Inc., 2015)
ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ይህ የያዕቆብ የማታለል ባህሪ በግልጽ ይታይ ነበር። ዘፍጥረት 25 ያዕቆብ በቤት ወጥ እየሰራ የነበረበትን ክስተት ይገልጻል (ዘፍጥረት 25:29) ። በሌላ በኩል ኤሳው ሜዳ ላይ አደን ለማደን ወጥቶ ነበር። ኤሳው ወደ ቤቱ ሲመለስ በጣም ተርቦ ነበርና ወንድሙን እየሰራው ከነበረው ወጥ እንዲሰጠው ጠየቀው።
የወንድሙን ረሀብ በመጠቀም ያዕቆብ ለኤሳው ብኩርናውን ሲሸጥለት ብቻ ከሰራው ወጥ እንደሚሰጠው ነገረው። ኤሳው ከሁለቱ ወንዶች ልጆች በኩር በመሆኑ ርስቱ ከያዕቆብ ይበልጥ ነበር። ያዕቆብ በዚህ ቅር ተሰኝቷል። ኤሳው የሚበላ ነገር ካላገኘ የሚሞት መስሎ ተሰማው፤ስለሆነም ለያዕቆብ በወጡ ምትክ ብኩርናውን እንደሚሰጠው ማለለት። ኤሳውም ይህን መሐላ በመማሉ ምክንያት ታናሹ ለታላቁ ይገዛል የሚለውን ለእናቱ ለርብቃ የተነገረውን የትንቢት ቃል በመፈጸም ለታናሽ ወንድሙ መብቱን በሕጋዊ መንገድ አሳልፎ ሰጠው። ይህ መብት ግን በተንኮል የተወሰደ ነበር።
የያዕቆብ የማጭበርበር እና የማታለል ባሕርይ ወንድሙን በችግር ጊዜ በያዘበት መንገድ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በአባቱ የእርጅና ዘመን ባደረገው ነገርም ታይቷል። ዘፍጥረት 27 ያዕቆብ የአባቱን የአይን ዕይታ ችግር እንዴት እንደተጠቀመበት ይተርካል። ይስሐቅ እያረጀ መሆኑን በማወቁ የበኩር ልጁን በልዩ በረከት ሊባርከው ፈልጎ ነበር። ይህ ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። የበኩር ልጁ በረከት በጣም አስፈላጊ ክስተት ነበር። ይህ በረከት ከአባት ብቻ የሚሆን ሳይሆን በአባቱ በኩል የመጣ የእግዚአብሔር በረከት ነበር። የኤሳው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዚህ በረከት ውስጥ ከአባቱ ቃላት ጋር በጥልቀት ተቆራኝቷል።
ይስሐቅ አብረው እንዲበሉ እና ይህን በረከት እንደ አባት እና ልጅ አድርገው እንዲያትሙት ልጁን ኤሳውን ወጥቶ ጥቂት ሥጋ አድኖ እንዲያመጣለት ነገረው። ይስሐቅ ልጁን ኤሳውን ሊባርከው መሆኑን ሲሰሙ ርብቃ እና ያዕቆብ ኤሳውን ለማታለል እና በረከቱን ለመውሰድ ዕቅድ አወጡ። ርብቃ ከመንጋው ውስጥ ለባሏ የተወሰነ ሥጋ አዘጋጀች። ያዕቆብ እንደ ወንድሙ ጸጉራም ሆኖ እንዲታይ የኤሳውን ልብስ ለብሶ ሰውነቱን በፍየል ቆዳ ሸፈነ። ያዕቆብም ስጋውን ወደ አባቱ አምጥቶ የወንድሙን በረከት ተቀበለ። ይስሐቅ ዓይኑ ታውሮ ስለነበር ለታናሹ ልጅ በረከቱን መስጠቱን አላወቀም ነበር። በዚህ መንገድ ያዕቆብ የኤሳውን በረከት ሰረቀበት።
ያዕቆብ ለወንድሙ እና እንደ በኩር ልጅ ላለው ቦታ አክብሮት ባለማሳየቱ እዚህ ጋር ቅር ተሰኝተናል። በዚህ መንገድ በማታለል አባቱን በእርጅና ዘመኑ ለማዋረድ ፈቃደኛ መሆኑን እንመለከታለን።
በድርጊቱ ምክንያት ያዕቆብ ከቤት ለመውጣት ተገደደ። ኤሳው በእሱ ላይ በጣም ስለተቆጣ አባቱ በሞተበት ቅጽበት ያዕቆብን ለመግደል ማለ። ኤሳው፣ቢያንስ ለአባቱ በቂ አክብሮት ነበረው፣በሕይወት እያለ ወንድሙን በመግደል ልቡን ለማሳዘን አልፈለገም። ያዕቆብ ከወንድሙ ቁጣ ለማምለጥ በእናቱ በኩል አጎቱ ወደሚኖርበት ወደ ካራን ምድር ሸሸ።
ያዕቆብ ወደ ካራን ምድር በተጓዘበት ጊዜ፤እግዚአብሔር በሕልም ለያዕቆብ ተናገረው፡
13…እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፦ የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤14 ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። 15 እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና። (ዘፍጥረት 28)
እነዚህ ቃላት በአውድ ውስጥ እንግዳ ናቸው። ያዕቆብ ከተናደደው ወንድሙ እየሸሸ ነው። ይህን እያደረገ ያለው እሱን በማታለሉ እና በረከቱን ለወሰደበት ነው። ሆኖም፣ ሕይወቱን ለማዳን ሲሸሽ፣ የበረከቱን ተስፋ ከሰጠው ጌታ እግዚአብሔር ጋር ተገናኘ። በዚህ አታላይ ሰው አማካኝነት የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉና። እግዚአብሔር ያዕቆብን የተናገረውን ሁሉ እስኪፈጽምለት ድረስ አይተወውም።
ገና ከመጀመሪያው ያዕቆብ የእግዚአብሔርን በረከት እንደሚቀበል ጌታ ለርብቃ አሳይቷት ነበር። ያዕቆብ ከወለደቻቸው ሁለት ልጆች የበለጠ ጠንካራ ይሆናል። እንደዚያ ስንል ያዕቆብ ከወንድሙ የተሻለ ነው ማለት ነውን? የእነዚህ ሁለት ወንዶች ልጆች ታሪክ ይህ እንዳልሆነ እንድናምን ያደርገናል። ያዕቆብ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ማክበር ያልቻለ አታላይ ነበር። እሱ ለራሱ ጥቅም ሲል ሰዎችን ሆን ብሎ ይጠቀማል። እንግዲህ እግዚአብሔር በዚያ ቀን በሕልም የባረከው ሰው ይህ ነው። ፍጽምና የጎደለው ሰው ነበር። የእግዚአብሔር በረከት ያዕቆብ ብቁ ከመሆኑ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም። ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት እና ጸጋ ድርጊት ነበር።
ያዕቆብ በካራን ምድር ሁለት ሚስቶችን አገባ። እግዚአብሔር ልያ እና ራሔል ከተባሉት ሚስቶቹ አሥራ ሁለት ልጆችን ሰጠው። እነዚህ ልጆች የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ናቸው። ታላቁ የእግዚአብሔር ዓላማ በአታላዩ በያዕቆብ በኩል ተፈጸመ።
የያዕቆብ ኃጢአተኛ ባህሪ ምንም ዋጋ እንዳላስከፈለው እንዳናስብ፣ ከያዕቆብ ሕይወት ጋር የሚዛመዱ ጥቂት ተጨማሪ ዝርዝሮችን ላስታውሳችሁ።የያዕቆብ አታላይነት የራሱ ውጤቶች ነበሩት።
በመጀመሪያ፣ያዕቆብ አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል የወንድሙን በቀል በመፍራት ይኖር ነበር። እግዚአብሔር ወደ ከነዓን ምድር በጠራው ጊዜ ያዕቆብ የተመለሰው በልቡ ታላቅ ፍርሃት ይዞ ነበር። ዘፍጥረት 32 የዚያን የፍርሃት መጠን ይገልጻል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከጌታ መልአክ ጋር ይታገል ነበር። ከወንድሙ ጋር የነበረው ይህ የተበላሸ ግንኙነት በጉልምስና ህይወቱ የተሸከመው ሸክም ሆኖ ቆይቷል።
ሁለተኛ፣ያዕቆብ ከአጎቱ ከላባ ጋር ይኖር ነበር። ላባ ያዕቆብ ለሰባት ዓመታት የሚያገለግለው ከሆነ ልጁን ራሔልን እንደሚድርለት ቃል ገብቶለት ነበር። ሆኖም በሠርጉ ምሽት ላባ በምትኩ ታላቋን ልያን ሰጠው። ነገሩ በታወቀ ጊዜ ላባ ያዕቆብ ለራሔል ሌላ ሰባት ዓመት እንዲሠራለት ጠየቀው። አታላዩ ራሱ ተታለለ። ያዕቆብ ከአማቱ ላባ ጋር በነበረው ግንኙነት ራሱ ብዙ ጊዜ ተታሏል። በዘፍጥረት 31 ላይ ለሚስቶቹ የነገራቸውን አዳምጡ፡
6 እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ። 7 አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉን ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። (ዘፍጥረት 31)
አታላይ የሆነው ያዕቆብ ዘወትር በእርሱ የሚጠቀምበት አማት ባለው በቤተሰብ ውስጥ ራሱን አገኘው። ይህ በጣም የተበላሸ የቤተሰብ ግንኙነትን አስከትሏል።
ሦስተኛ ፣ የያዕቆብ ሚስቶች ሁልጊዜ እርስ በእርስ በእርሳቸው ይፎካከሩ ነበር። ራሔል እና ሊያ ሁለቱም ያዕቆብን ትኩረት ለመሳብ ይታገሉ ነበር። ራሔል ልጅ መውለድ ስላልቻለች በምሬት ታጉረመርም ነበር። ሊያ ሁልጊዜ የማትወደድ ሚስት እንደሆነች ይሰማት ነበር። የያዕቆብ ሚስቶቹ እርስ በእርስ በነበራቸው ሙግት ምክንያት በመሃል ተይዞ ነበር። ራሔል በአገልጋይዋ ባላ በኩል እግዚአብሔር ልጅ ሲሰጣት የተናገረችውን አድምጡ፡
8 ራሔልም፦ ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው። (ዘፍጥረት 30)
የያዕቆብ ቤተሰብ ችግሮች በሚስቶቻቸው የሚያበቃ አልነበረም። ዘፍጥረት 34 ሴት ልጁ ዲና በሚኖሩባት ምድር ከአንዳንድ ወጣት ልጃገረዶች ጋር እንደወጣች እና ሴኬም ከሚባል ወጣት ጋር እንዴት እንደተገናኘች ይተርካል። ሴኬም ዲናን በማታለል ደፈራት።
የያዕቆብ ልጆች በእህታቸው ላይ የሆነውን ነገር በሰሙ ጊዜ በጣም ተቆጡ። ሴኬም እና አባቱ ስለዚያ ክስተት ያዕቆብን ለማግኘት ወደ እርሱ መጡ። የሴኬም አባት ሔሞር ያዕቆብን የሙሽራ ዋጋ እንዲወስንለት እና ልጁ ሴኬም ዲናን ያገባ ዘንድ ጠየቀው።የያዕቆብ ልጆች ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ አዳምጡ፡
13 የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤ 14 እንዲህም አሉአቸው፦ እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና።15 እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤ (ዘፍጥረት 34)
በጉዳዩ ተስማምተው ሴኬምና ሔሞር ወደ ቤታቸው ሄደው የከተማቸውን ወንዶች ሁሉ እንዲገረዙ አደረጉ። ነገር ግን አስተውሉ፣ ዘፍጥረት 34:13 የያዕቆብ ልጆች በጥያቄአቸው አታላዮች እንደነበሩ ይነግረናል። ግርዛቱ ከተፈጸመ ከሦስት ቀናት በኋላ ስምዖንና ሌዊ ሰይፋቸውን ይዘው ሰዎቹ ገና ከቁስላቸው ሳያገግሙ ሁሉንም ሲገድሉ ያ ተንኮል ተገለጠ።
የያዕቆብ አታላይነት ወደ ልጆቹ ተላልፎ ነበር። በዚህ ሁኔታ ያዕቆብ ለዚህ የሚከፍለው ከባድ ዋጋ ነበር። በዚያ ቀን ለልጆቹ ሲናገር እንዲህ አለ፡
30 ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ፦ በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ። (ዘፍጥረት 34)
በዘፍጥረት 35:22 ላይ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል ከቁባቱ ጋር በመተኛት አባቱን እንዴት እንዳዋረደ እናነባለን። ራሱ አባቱን በእርጅና ዕድሜው ያላከበረ ሰው አሁን ይህንን ህመም እና ውርደት በገዛ ልጁ በኩል ደረሰበት።
ያዕቆብ፣ዘወትር ከሚያታልለው ከላባ ጋር ባለው ግንኙነት ችግር ላይ ነበር። እንዲሁም ሁልጊዜ ከሚጣሉ እና አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ለመጠቀም ሁልጊዜ እየሞከሩ ካሉ ሁለት ሚስቶች ጋር ይኖር ነበር። ልጆቹ በውስጣቸው ይህ የማታለል ተፈጥሮ ነበራቸው፤ስለሆነም በአንድ ከተማ ውስጥ ላሉት ወንዶች ግድያ ተጠያቂዎች ነበሩ። ይህ ማታለል ከአከባቢው ህዝቦች ጋር የነበረውን ግንኙነት አበላሽቷል። የበኩር ልጁ የሆነው ሮቤል ከቁባቱ ጋር በመተኛት አዋርዶታል።
እግዚአብሔር ሊባርከው የወሰነው ሃገር አባት ለመሆን የምትመርጡት ሰው ይህ ይሆን? ቤተሰቦቹ ችግር ውስጥ ያሉ ይመስላል። የግል ሕይወቱ መሆን ያለበት ቦታ አልነበረም። በማህበረሰቡ ውስጥ የሰጠው ምስክርነት አጠያያቂ ነበር። ሆኖም በዚህ አታላይ ሰው አማካኝነት አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ተወለዱ።
ከሴኬም እና ዲና ክስተት በኋላ እግዚአብሔር ያዕቆብን አከባቢውን ለቆ ወደ ቤቴል እንዲሄድ ተናገረው (ዘፍጥረት 35:1) ። ዘፍጥረት 35:5 ስለዚያ ጉዞ ምን እንደሚነግረን አስተውሉ፡
5 ተነሥተውም ሄዱ፤የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። (ዘፍጥረት 35)
የትኛውም ሰው ሊያጠቃቸው እንዳይደፍር የያዕቆብ ልጆች በሚጓዙበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ ይጠበቃቸው ነበር።
እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ወደ እስራኤል ለወጠው፣ ትርጓሜውም “ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገል” ማለት ነው። ነገር ግን ከዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ለታገለው ሰው አንድ የተስፋ ቃል ተሰጠው።
10 እግዚአብሔርም፦ ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11 እግዚአብሔርም አለው፦ ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ። (ዘፍጥረት 35)
እግዚአብሔር ለያዕቆብ ያቀረበው ጥሪ ፍሬያማ እና መብዛት ነበር። የአባቶቹ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ምድርን እና ዘርን ይሰጠዋል። በዚያ ዘር በኩል ምድር ሁሉ ይባረካል።
የያዕቆብ ምስክርነት ከፍጹምነት የራቀ ነው። በግለሰብ ደረጃ በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ነበሩት። ቤተሰቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር። በልጆቹ ድርጊት ምክንያት በማህበረሰቡ ዘንድ የነበረው ምስክርነት ተበላሽቷል። እግዚአብሔር ይህን ሰው “ፍሬያማ እንዲሆን እና እንዲበዛ” ጠራው። እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ጠብቆት በእርሱ ለመጠቀም መረጠ። ያዕቆብ ሕይወቱን ወደ ኋላ ሲመለከት ፣ ሁሉንም ድክመቶቹን እንደሚያውቅ እርግጠኛ ነኝ። በእነዚያ ድክመቶች በግል እና በቤተሰብ ሕይወቱ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን አሳዛኝ ውጤት ተመልክቷል። እንግዲህ በዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ቢያልፍም፣ ጌታ እሱን ለመባረክ እና ለመጠቀም የመረጠውን አስደናቂ የእግዚአብሔር ጸጋ ያውቅ ነበር።
ለምልከታ፡
• ከርብቃና ከይስሐቅ ከተወለዱት መንትዮች ታናሽ ለሆነው ለያዕቆብ የእግዚአብሔር ዓላማ ምን ነበር?
• ያዕቆብ የታላቅ ወንድሙን የኤሳውን በረከት እና ብኩርና እንዴት ወሰደ?
• ያዕቆብ በአታላይነቱ ምክንያት ከቤት ለመውጣት ተገዶ ነበር። ወደ ካራን ምድር ሲሄድ ጌታ እንዴት ተገናኘው? እግዚአብሔር ለያዕቆብ የገባው ቃል ምን ነበር?
• በያዕቆብ ቤተሰብ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደነበር ግለጹ። በዚህ መልስ ውስጥ ሚስቶቹን እና ልጆቹን አስቧቸው።
• የያዕቆብ ልጆች ሴኬምንና የከተማዋን ሰዎች ከገደሉ በኋላ እግዚአብሔር መገኘቱን ለእነርሱ እንዴት ገለጸ? ዘፍጥረት 35:5ን ተመልከቱ።
• ያዕቆብን ለበረከትና ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያበቃው ምን ነበር? እንግዲህ ይህ ሰው የእግዚአብሔር በረከት እና የተስፋ ቃል መጠቀሚያ መሣሪያ እንዲሆን ትመርጡታላችሁን?
• የያዕቆብ አታላይነት በግል ሕይወቱ ያስከተላቸው ውጤቶች ምን ነበሩ?
ለጸሎት፡
• ከእግዚአብሔር ቃል ትምህርት እና ለሕይወታችሁ ካለው ዓላማ ጋር የማይጣጣም ማንኛውንም ነገር እንዲገልጥ ጌታን ጠይቁ።
• የግል ጉድለቶች እና ድክመቶች ቢኖርባችሁም እርሱ ምህርት ስላደረገላችሁ ጌታን አመሰግኑ።
• ቤተሰባችሁን ወደ እሱ ለማሳደግ ባላችሁ መሻት ጌታ ጥበብን እንዲሰጣችሁ ጠይቁ።
• በኃጢአታችሁ ምክንያት የመጣባችሁን ውጤቶች መጋፈጥ ነበረባችሁን? እርሱን በሚያከብር መንገድ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በአግባቡ ለመጓዝ ጌታ ብርታትን እንዲሰጣችሁ ጠይቁ።
• ከእርሱ ክብር ስንጎድል እኛን ስለማይተወን ጌታን አመስግኑት።
• ምንም እንኳን ድካም ቢኖርበትም የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ይሆን ዘንድ ያዕቆብን ስለተጠቀመበት መንገድ ጌታን አመስግኑት።
ምዕራፍ 2 - ሃገር እና ሕዝብ የሌለው ሰው
የሙሴ ሕይወት የጀመረው በግብፅ ምድር ነበር። አባቱ ሌዋዊ ነበር (ዘጸአት 2፡1) ስለዚህ እርሱ የተወለደው እግዚአብሔር የክህነቱ ወኪል እንዲሆኑ በመርጠው ነገድ ውስጥ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የራሳቸው መሬት አልነበራቸውም። በመሠረቱ፣ ሙሴ በተወለደ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በግብጻውያን ዘንድ እንደ ባሪያ ሆነው ሲኖሩ እና በደል ይደርስባቸው እና ይሰቃዩ ነበር። ይህ በደል በጣም ጨካኔ የሞላበት ከመሆኑ የተነሳ ፈርዖን ከእስራኤል ሴት የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ አባይ ወንዝ እንዲጣል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘፀአት 1፡22)
የሙሴ እናት ከግብፃውያን ባለሥልጣናት እሱን ለመደበቅ የተቻላትን ሁሉ ሞክራ ነበር፣ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በአባይ ወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው።በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም። ወስዳም እንደራሷ ልጅ አድርጋ ለማሳደግ ወሰነች (ዘጸ 2፡3-11) ። ሙሴ እንደ ግብጻዊ ከወገኖቹ ተለይቶ አደገ። ይህ ከገዛ ወገኖቹ መሰደዱ ደስ የሚያሰኝ ባይሆንም ሙሴን ያስጨንቀው ነበር።
ዘጸአት 2፡11፣12 ሙሴ ባደገ ጊዜ የራሱን ህዝብ ለማየት እንዴት እንደ ወጣ ይተርካል። በዕለቱ ያየው ነገር ግን አበሳጨው። አንድ ግብፃዊ አንድ እስራኤላዊን ሲደበድብ ተመለከተ። ዘጸአት 2፡12 በምላሹ ያደረገውን ይናገራል:
12 ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። (ዘጸአት 2)
ሙሴ ይህን ግብፃዊ የገደለው እስራኤላዊውን ባሪያ ስለደበደበ ነው። እሱ ያደረገው ስህተት መሆኑን ያውቅ ነበር። ምንባቡ እንደሚነግረን “ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው።” ይላል። በግልጽ እንደሚታየው ሙሴ ለመያዝ አልፈለገም ነበር። የሐዋርያት ሥራ 7:23-25 ሙሴ ይህን ግብፃዊ ለመግደል ለምን እንደፈለገ ይነግረናል።
23 ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። 24 አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። 25 ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
ሙሴ ለሕዝቡ ሸክም ስለነበርው ሊረዳቸው እንደሚችል ያምን ነበር። በፈርዖን ሴት ልጅ ያደገ እንዲሁም በሃገሩ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ስልጣን ያለው ሰው ነበር። በእስራኤል ያሉትን ወንድሞቹንና እህቶቹን ሊረዳቸው እንደሚችልና እሱ ከጎናቸው መሆኑን ለማሳየት ፍላጎት ነበረው።
ይህ የሙሴ ድርጊት የሚያሳየን በግብፅ ምቾት ውስጥ ቢያድግም ልቡ ግን በዚያ እንዳልነበረ ነው። እሱ የእስራኤል ስለሆነ ወደ ወገኖቹ ተመልሶ በችግራቸው ጊዜ ሊረዳቸው ይፈልግ ነበር። ከውጭ የሚታየው የስደት ኑሮው ምቹ ቢሆንም ዳሩ ግን በውስጣዊው ስሜቱ እና መንፈሱ ሙሴ ደስተኛ አልነበረም። ሙሴ ራሱን ከህዝቡ እንደተለየ ስደተኛ ይመለከት ነበር።
በሌላ አጋጣሚ ወደ ወገኖቹ ሲመለስ፤ሙሴ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ተመለከተ። እነዚህን ሰዎች ለምን እርስ በርሳቸው እንደሚጣሉ ጠየቃቸው። ሆኖም ምላሻቸው ለሙሴ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡
14 ያም፦ በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው። ሙሴም፦ በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል ብሎ ፈራ። (ዘጸአት 2)
በዚያ ቀን እነዚያ ቃላት በሁለት ምክንያቶች የሙሴን ነፍስ በጥልቀት ወግተውት መሆን አለባቸው። በመጀመሪያ፣ የእስራኤላዊው ቃል ሙሴ ግብፃዊውን እንደገደለ እና በአሸዋ ውስጥ እንደሸሸገው ማወቁን ይገልጣል። እስራኤላውያን ስለዚህ ጉዳይ ካውቁ ብዙም ሳይቆይ የግብፅ ባለሥልጣናትም ያውቁታልና። ሙሴ በነፍስ ግድያ ጥፋተኛ ነበር ስለሆነም ቢያዝ የሚመጣበትን መዘዝ ይፈራ ነበር።
በእኛ ላይ አለቃ እና ዳኛ ማን አደረገህ? የሚለው የዚህ ሰው ቃላት በጣም ጎጂ የሆነበት ሁለተኛው ምክንያት የእስራኤል ሕዝብ ልብ ለእርሱ ያለውን ሃሳብ ስለገለጡ ነው። እስራኤል ሙሴን እንደ እንደ አለቃቸው እና ተከላካይ አደርገው አልተቀበሉትም። ስለሆነም ከእሱ ጋር ምንም ለማድረግ አልፈለጉም። በእነርሱ እይታ፤እርሱ የእነርሱ አባል አይደለም። ብዙ ሰቆቃ እየደረሰባቸው ለፈርዖን እንዲሠሩ ሲገደዱ እርሱ በቅንጦት ይኖር ነበር። ሙሴ ያደገው ጠላቶቻቸው በሆኑ ሰዎች ነው፣እነሱም እንደ አንዱ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ስላልተቀበሉትም የእርሱን እርዳታ አልፈለጉም።
ሙሴ በዚያ ቀን አገር የሌለው ሰው መሆኑን ሳይገነዘብ አልቀረም። እስራኤል እርሱን አልተቀበለውም። ፈርዖን ግብጻዊውን በመግደል ጥፋተኛ መሆኑን ሲያውቅ እሱን ለመግደል መፈለጉ አይቀርም። ሙሴ በስደት ከግብፅ ለመውጣት ተገደደ። ቀጣዮቹን አርባ ዓመታት ሕይወቱን በባዕድ የምድያም ምድር በጎችን በማገድ ያሳልፋል። ሙሴና ከምድያም ሚስቱ የመጀመሪያ ልጃቸውን በወለዱ ጊዜ ሙሴ ጌርሳም ብሎ ጠራው። ይህን ስም የሰጠበትን ምክንያት አስተውሉ፡
22 ወንድ ልጅም ወለደች፦ በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። (ዘጸአት 2)
ሙሴ የስደት ሕይወቱን በጣም ያውቅ ነበር። እሱ አገር የሌለው እንዲሁም፣ እርሱን ከማይፈልገው እና ሊገድለው ከሚፈልገው ሃገር የተሰደደ ሰው ነበር። በምድያም ምድር እረኛ ሆኖ ለአርባ ዓመታት በስደት ኖረ።
ሙሴ ሰማንያ ዓመት እስኪሞላው እና ጌታ እግዚአብሔር እስከተገለጠለት ጊዜ ድረስ ከዚያ አልወጣም ነበር። ዘጸአት 3 ሙሴ በጎቹን እንደሚጠብቅ እና በበረሃ ውስጥ ቁጥቋጦ በእሳት የተቃጠለበትን ሁኔታ ይተርካል። እግዚአብሔር ከዚያ ቁጥቋጦ ውስጥ ሙሴን ተናገረው።
4 እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ፦ ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ። 5 እርሱም፦ እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው። 6 ደግሞም፦ እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። (ዘጸአት 3)
እግዚአብሔር ራሱን ለሙሴ እንዴት እንዳስተዋወቀ አስተውሉ። “እኔ የአባትህ አምላክ ፣ የአብርሃም አምላክ ፣ የይስሐቅ አምላክ እና የያዕቆብ አምላክ ነኝ። እነዚህ ቃላት ሃገር አልባ ለሆነ እና የባለቤትነት ስሜት ለማይሰማው ስደተኛ ሰው ያላቸውን ትርጉም አቅልለን ማየት አንችልም። እግዚአብሔር በዚያ ቀን ሙሴ የአባቱ የአብርሃም አምላክ መሆኑን አስታወሰው። ይህም ሙሴን ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ለይቶታል። ለአርባ ዓመታት እንደ ግብፃዊ ሆኖ አደገ። ከዚያም በምድያም ምድር እረኛ ሆኖ ሌላ አርባ ዓመት ኖረ። እግዚአብሔር ግን ማንነቱንና ዓላማውን እያስተማረው ነው። እሱ የእስራኤላዊው የአብርሃም ልጅ መሆኑን ያስታውሰዋል።ይህ በእግዚአብሔር ፊት ማንነቱ ነበር።
ይህ ለሙሴ ልዩ ቀን መሆን አለበት። በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብ እንዳለው ከእግዚአብሔር በመስማት አረጋገጠ። አስተውሉ፣እግዚአብሔር በዚህ ብቻ አያቆምም። በመቀጠልም ሕዝቡ በግብፅ ውስጥ ስለገጠሙት ችግሮች ከሙሴ ጋር ተነጋገረ። እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩኸት ሰምቶ በዚያም አንድ ነገር ሊያደርግ ነው። በፈርዖን ፊት ሕዝቡን እንዲወክል እንደመረጠው ለሙሴ ተናገረው። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ በጣም ኃያል በሆነ መሪ ፊት ጉዳያቸውን የሚያቀርበው እሱ ይሆናል። እግዚአብሔር ሙሴ የእስራኤል ልጅ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ፣ ነገር ግን ለዚያ ሕዝብ የእሱ ወኪል ይሆን ዘንድ አረጋገጠለት።
እኔ ስለ እናንተ አላውቅም፣ነገር ግን እኔ ሙሴን ብሆን እንደዚህ ላለው ተግባር ብቁ እንዳልሆንኩ እርግጠኛ ነኝ። በእርግጠኝነት ከሙሴ በተሻለ ሊወክላቸው ከሚችል ሰው ላለፉት ሰማንያ ዓመታት ከህዝቡ መካከል የኖረ ሰው መሆን አለበት። ለዚህ ወደ ሕይወቱ ለመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ ሙሴ የሰጠውን ምላሽ አስተውሉ፡
11 ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። (ዘጸአት 3)
በዚያ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም ፣ ከዚህ ጥሪ ጋር ይታገል ነበር። ከዚህ በፊት የእስራኤል ሕዝብ ለአርባ ዓመት እርሱን አልተቀበሉትም ነበር። ግብፅ እንደ ነፍሰ ገዳይ እና ከሃዲ ትመለከተው ነበር። ስለመናገር ችሎታውን ጥያቄ አቅርቧል። ላለፉት አርባ ዓመታት እረኛ ስለነበር የአንድ ሀገር መሪ ለመሆን ብቁ እንደሆነ አልተሰማውም።
ወደ ሕይወቴ የመጣውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ስመለከት እንደ ሙሴ የተሰማኝ ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ቃሉን እጽፍ እና አስተምር ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እግዚአብሔር እኔ የማዘጋጃቸው መጽሐፎች ተተርጉመው ወደ ተለያዩ አገሮች እንዲላክ ይፈቅድ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ይህን አገልግሎት ሊያገለግሉ የሚችሉ ከእኔ የበለጠ ብቃት ያላቸው የሚመስሉ በርካታ ሰዎች አሉ። መልሱ ሁልጊዜ እግዚአብሔር ወደጠራኝ ወደ እውነታው ይመልሰኛል። ወደ ሕይወቴ የመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ እንጂ የእኔ ብቃት እንዳልሆነ ተገንዝቤአለሁ። ብቁ የሆንኩት በእኔ ልምድ ወይም ችሎታ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለጠራኝ ነው። እኔ እንደ ሙሴ፣ለሥራው ብቁ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር፣ ነገር ግን በሕይወቴ የእግዚአብሔር ጥሪ እና ዓላማ በመተማመን እወጣለሁ።
ሙሴን በቀጣዮቹ ዓመታት ስንመለከት፤ወደ ግብፅ እየተመለሰ ያለን ዓይናፋር ሰው እናስተውላለን። የእግዚአብሔርን መሪት እየተከተለ ለፈርዖን እና ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን ሲናገር እናያለን። ሙሴ ጥበብን እና ምሪትን ለመፈለግ በየጊዜው ወደ ጌታ ፊት ሲሄድ እንመለከታለን። እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ሲሠራ እና ግብፅን ሲመታ እንዲሁም መላው ሕዝብ ከባርነት ነጻ ሲወጣ እናያለን። እስራኤላውያንን ወደ ደኅንነት ለመምራት የባሕሩ ውኃ ሲከፈል የእግዚአብሔር ተአምራዊ ኃይል ሲገለጥ እናያለን። ከሁለት ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች እና ለእንስሳዎቻቸው የእግዚአብሔርን ዕለታዊ አቅርቦትን እናስተውላለን። እግዚአብሔር ይህንን ሃገር አልባ ስደተኛ ሰው ሕዝቡን የሚተዳደሩበት ሕግጋት ወዳለው ሉዓላዊ ሃገር ለማቅናት ይጠቀምበታል።
ሙሴን ለሃገር ግንባታ ተግባር ብቁ ያደረገው ምንድ ነው? አገልግሎቱን ይህን ያህል ፍሬያማ ያደረገው ምንድን ነው? የእግዚአብሔር ምርጫ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? በግብፅ ሃገር የነበረው ተጽዕኖ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። እግዚአብሔር ያንን ከእርሱ ገፎታልና። እንዲሁም ከግብፅ ቅጣት አምልጦ ስለነበር እስራኤል ያለፈበት የባርነት መከራ አላጋጠመውም። የእስራኤላውያን ክብርን በማግኘቱም አልነበረም፤ምክንያቱም ከግብጻውያን እንደ አንዱ አድርገው ስለተመለከቱት አልተቀበሉትም ነበርና። በተፈጥሮአዊው ችሎታው የመጣ አልነበረም ምክንያቱም ወደዚህ አገልግሎት ከመጠራቱ በፊት ያ ተፈጥሮአዊ ችሎታው በእድሜ መግፋት ምክንያት እስኪቀንስ እና ሰማንያዎቹ እድሜ ላይ እስኪደርስ ድረስ እግዚአብሔር ይጠብቀው ነበርና። ስለ አገልግሎት ፍሬያማነት ሰው የሚሰጣቸውን ምክንያቶችን ከልብ መፈለግ እንዴት ቀላል ነው። በመጨረሻ ግን ፣ በሙሴ ሕይወት የነበረው ፍሬያማ አገልግሎት ከማንኛውም የግል ብቃቶች ይልቅ ከእግዚአብሔር ጸጋ ጋር የሚገናኝ ነበር። እግዚአብሔር ለዚህ ተግባር ስለመረጠው ፍሬያማ ነበር። ሙሴ እግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል እንኳን ፈቃደኛ አልነበረም። በእግዚአብሔር እና በሙሴ መካከል የተደረገውን ውይይት አዳምጡ፡
አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። (ዘጸአት 3:10)
ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። (ዘጸአት 3:11)
እርሱም፦ በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ… (ዘጸአት 3:12)
እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። (ዘጸአት 3:14)
እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘እኔ እኔ ነኝ ‘(ዘጸአት 3:15)
ሙሴም መለሰ፦ እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም፦ እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም ይሉኛል አለ። (ዘጸአት 4:1)
እግዚአብሔርም፦ ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት? አለው። እርሱም፦ በትር ናት አለ። ወደ መሬት ጣላት አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ (እባብም ሆነች) ። (ዘጸአት 4:2-3)
ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። (ዘጸአት 4:10)
እግዚአብሔርም፦ የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው። (ዘጸአት 4:11-12)
እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ አለ። (ዘጸአት 4:13)
ሙሴ ከፊቱ ላለው ሥራ ራሱን ብቁ ሆኖ እንዳላገኘው ትንሽ ጥርጣሬ ሊኖር ይችላል። በዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ባደረገው ክርክር፣ በራሱ ብቁ ስለመሆኑ እምነት አልተሰማውም፣ እግዚአብሔር ለሥራው የሚያስፈልገውን ሁሉ እየሰጠው ወደ እውነታው ማምጣቱን ቀጥሏል። ሙሴ እግዚአብሔር ለጥሪው እና ሥራው የሚያስፈልገውን አሟልቶ ስለሰጠው ስኬታማ ሆኗል። እግዚአብሔር ሙሴን የመረጠው ባሉት ምርጥ ብቃቶች ምክንያት አይደለም፤ሙሴ ስለዚህ ጉዳይ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ንግግር በጣም ግልፅ ነው።
ሃገርን ለመገንባት እግዚአብሔር ስደተኛ እንዲመርጥ ያደረገው ምንድን ነው - ጸጋው ብቻ ነው። እግዚአብሔር መላውን ዓለም የሚባርክበትን ታላቅ ሕዝብ ለመምራት የተሰበረውን ሰው መጠቀምን መረጠ። ለሙሴ ኃይል የሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ወዴት መሄድ እንዳለበት ሳያውቅ የሚያስፈልገውን ጥበብ የሰጠው ጸጋው ነው።
እንዲህ ባለው ፍሬያማ አገልግሎት ሙሴን ለመባረክ እግዚአብሔር ላይ ተጽዕኖ ያደረገውን ነገር በሙሴ ህይወት ውስጥ ለማግኘት የምንፈልገውን ያህል፣እውነታው ሙሴ ነገሮችን በዚህ መንገድ አለማየቱ ነው። ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበርና። እግዚአብሔር በጸጋው እንደ አምባሳደር እና የአንድ ሃገር መሪ አድርጎ የመረጠው ቤት አልባውን ስደተኛ ነበር።
ለምልከታ፡
• ሙሴ ከገዛ ወገኖቹ እንዴት ተወሰደ?
• ሙሴ ግብጻዊ ሆኖ በማደጉ ደስተኛ ነበር? የእሱ ታማኝነት የት ነበር?
• እስራኤል ሙሴን እንዴት ይመለከተው ነበር?
• ሙሴ በምድያም ምድር ሲኖር ምን ይሰማው እንደነበር የበኩር ልጁ ስም ምን ያመለክታል?
• ሙሴ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል ብቁ ሆኖ ተሰማውን? አብራሩ።
• የሙሴ ብቸኛው ትክክለኛ መመዘኛ በሕይወቱ የመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ ብቻ ነው ማለት ትክክል ይሆናልን? ይህ በቂ ነበር?
• ለመንግሥቱ ፍሬያማ እንዲያደርገን ከራሳችን አንድ ነገር መፈለግ እንደሚያስፈልገን የሚሰማን ለምንድ ነው? የሙሴ ፍሬያማ አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው የንጹህ ጸጋ ተግባር እስከ ምን ድረስ ነበር?
ለጸሎት፡
• እኛ የማንቀበላቸውን ሰዎች ለመጠቀም ፈቃደኛ በመሆኑ ጌታን ለማመስገን ትንሽ ጊዜ ውሰዱ።
• በሕይወቱ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል ሲታገል ለነበረው ሙሴ ስላሳየው ትዕግሥት ጌታን አመስግኑ። በሕይወታችሁ ከመጣው ከእግዚአብሔር ጥሪ ጋር ታግላችኋልን?
• እግዚአብሔር ለሰጠን አገልግሎት በተፈጥሮ ብቁ ባንሆንም፣እርሱን ለማገልገል የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን በእርሱ በመታመን ጌታን አመስግኑት።
• በሕይወታችሁ ወደ መጣው ወደ እርሱ ጥሪ ለመውጣት እንድትችሉ ጌታ ጸጋ እንዲሰጣችሁ ጸልዩ።
ምዕራፍ 3 - በቀለኛው ብርቱ ሰው እና የእስራኤል ጠላቶች ሽንፈት
አንዳንድ ጊዜ መንግሥቱ ላይ ኃይለኛ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ሰዎች ወደ ጌታ መቅረብ እንዳለባቸው ይሰማናል፣አለበለዚያ እንዴት በአገልግሎት ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ሃሳብ ስኬትን ከታማኝነት ጋር አቆራኝቶ ይገልጻል። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ አንድ ነገር ስለተመለከተ ይጠቀምብናል ከሚል ስሜት የመጣ ነው። በአገልግሎት ውስጥ ፍሬያማነት የእኛ መልካም ጥረት ወይም በስጦታዎች እና ተሰጥኦዎች አጠቃቀም ምክንያት የምናገኘው ነገር ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ተግባር መሆኑን ማየት ይሳነዋል። እስቲ በእስራኤል ውስጥ ሳምሶን የተባለውን የአንድ መሳፍንት ሕይወት እንመልከት።
ሳምሶን የተወለደው ፍልስጤማውያን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ከባድ ችግር እየፈጠሩ በነበረበት ወቅት ነበር። መሳፍንት 13:1 የሚናገረውን አዳምጡ፡
1 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። (መሣፍንት 13)
ይህ ጥቅስ ሳምሶን ይኖርበት በነበረው ዘመን ሁለት ነገሮችን ያሳየናል። አንደኛ፣ የእስራኤል ሕዝብ ከጌታ እግዚአብሔር በመፍራት አይመላለስም ነበር። ሁለተኛ፣ በኃጢአታቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ላይ ነበር። ይህ ለአርባ ዓመታት ያህል ሲጨቁኗቸው በነበሩት ፍልስጤማውያን መልክ የመጣ ነበር።
ሳምሶን የተወለደው ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ ባልተጠቀሰ ሴት ነው። እርሷም የማኑሄ ሚስት ነበረች። የማኑሄ ሚስት መካን ነበረች ነገር ግን አንድ ቀን የጌታ መልአክ ተገልጦላት እንደምትፀንስና ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት (መሳፍንት 13: 3) ። መልአኩ ለሳምሶን እናት ይህ ልጅ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለጌታ ተለይቶ እንደሚኖር ነገራት።
3 የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፦ እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4 አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ። 5 እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።
የማኑሄ ሚስት ይህ የልጅዋ መለየት ለሕይወት ዘመን ሁሉ እንደሚሆን በመረዳት ለባሏ የነገረችው በጣም ግልፅ ነው፡
7 እርሱም፦ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች። (መሣፍንት 13)
እግዚአብሔር በሳምሶን ላይ ያኖረውን ልዩ መለያዎችን አስተውሉ። በመጀመሪያ፣ የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር በጭራሽ አይጠጣም። ሁለተኛ፣ርኩስ የሆነ ነገር ፈጽሞ አይበላም። ሦስተኛ፣በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት። እነዚህ ለጌታ የመለየቱ ምልክቶች ነበሩ፤ስለሆነም ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእነዚህ መመዘኛዎች እንዲኖር ይጠበቃል። ጌታ ለሳምሶን በጣም የተለየ ዓላማ እንዳለው ከመልአኩ ቃል አስተውሉ። እሱ እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ለማዳን ሳምሶንን ሊጠቀም ዓላማ ነበረው። ሳምሶንም ለዚህ ዓላማ የተወለደ ልዩ ልጅ ነበር።
ሳምሶን ሲያድግ ወደ ፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደ ተምና ወረደ። በእስራኤል ጠላቶች ከተማ ለምን እንደነበረ አልተነገረንም፤ዳሩ ግን እዚያ በነበረበት ጊዜ እርሱን በፍቅር የሳበች አንዲት ፍልስጥኤማዊ ሴት አገኘ። ወደ እስራኤል በመመለስ ለአባቱ እና እናቱ ሊያገባት እንደሚፈልግ ነገራቸው። ይህም የወላጆቹን ልብ አሳዘነ። እስራኤላውያን ወንዶች ባዕድ ሚስቶችን ማግባት አይገባቸውምና። ፍልስጤማውያን የእስራኤል ጠላቶች ስለነበሩ እና ሳምሶን ደግሞ ከዚህ ጠላት እንደሚያድናቸው የጌታ መልአክ አስቀድሞ ነግሯቸው ስለነበር ይህ ጉዳይ ወላጆቹን የበለጠ አሳሰበ። እዚህ ሳምሶን ጠላቱን ለማግባት ሲፈልግ እንመለከታለን። ይህም ጠላትን የቤተሰቡ አባል ያደርጋል። በዚህ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን አለመታዘዝ ጥሩ ነገር ሊሆን እንደሚችል ወላጆቹ አላዩም ነበር።
በዚህ ጋብቻ ላይ ስጋት ቢኖራቸውም፣የሳምሶን ወላጆች የወጣት ፍልስጤማዊቷን ቤተሰብ ለማነጋገር አብረውት ሄዱ። በመንገዳቸው ላይ የአንበሳ ደቦል እያገሳ ወደ እርሱ ደረሰ፤ ሳምሶንም፤ በባዶ እጁ ገድሎ ቆራረጠው (መሳፍንት 14፡5-6 ተመልከቱ) ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሲመለስ ሳምሶን የገደለውን የአንበሳ አካል ለማወቅ ጓጉቶ ነበር። ፈልጎም ሄዶ አገኘው። በዚህ የሞተ አንበሳ አካል ውስጥ የንብ መንጋ ተመልክቶ ሳምሶን ማርን በእጆቹ ወስዶ መንገዱን ቀጠለ። ጥቂት ማር ለወላጆቹ ሰጠ ፣ ነገር ግን ከሞተ አንበሳ አስከሬን እንደ ወሰደው አልነግራቸውም (መሳፍንት 14፡9 ተመልከቱ) ።
በዚህ ረገድ ጉልህ የሆነው ነገር ሳምሶን የሞተውን እንስሳ አካል መንካቱ ነው። ናዝራዊ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ሲለይ የተሰጠው አንዱ ግዴታ ርኩስ ነገር እንዳይነካ ነው። ይህ የሞተ እንስሳ ርኩስ ነበር። ማርን ከየት እንዳገኘ ለወላጆቹ ያለመናገሩ እውነታ ቃል ኪዳኑን በእግዚአብሔር ፊት እንደሚያፈርስ በማወቁ ምክንያት እንደሆነ ሊጠቁም ይችላል። ይህ እሱን የሚያሳስበው አይመስልም።
ሳምሶን ቃል ኪዳኑን በቁም ነገር አለመውሰዱ ብቻ ሳይሆን ይህን ቃል ኪዳን በማፍረሱ የተደሰተ ይመስላል። ቤተሰቡ በተምና ጋብቻውን ሲያከብሩ ሳምሶን እና ሠላሳ ጓደኞቹ በአንድነት እየበሉ ነበር። ሳምሶን ከእነርሱ ጋር ውርርድ አደረገ። እንቆቅልሹን መፍታት ከቻሉ ለእያንዳንዳቸው ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እንደሚሰጣቸው ነገራቸው። ካልቻሉ እያንዳንዳቸው ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ይሰጡታል።
እንቆቅልሹ በጣም ቀላል ነበር፡
14 እርሱም፦ ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፥ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም። (መሣፍንት 14)
ሳምሶን ለእግዚአብሔር የገባውን ቃል በማፍረሱ ኩራት የተሰማው ይመስላል። በዚህ ክፍል እሱ ከሠራው ነገር ተነስቶ ቀልድ ሲቀልድ እንመለከታለን። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ቃል ኪዳናቸውን በቁም ነገር የወሰዱ ሰዎች ይህንን እንደ ቀልድ አያዩትም። እዚህ ሳምሶን የሚያፍርበት ምንም ስሜት የለውም።
የእንቆቅልሹን መልስ ለማግኘት የሳምሶን ጓደኞች እጮኛውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚገድሉ አስፈራሩ። መልሱን እንዲነግራት ሳምሶንን ስትገፋው እሱም ነገራት። እሷም ለጓደኞቹ ነገረቻቸው፤ ከዚያም የእንቆቅልሽ መልሳቸውን የሚመልሱበት ቀን ሲደርስ ጥያቄዎቹን በትክክል መለሱ። ውርርዱን ለመክፈል ሳምሶን ወጥቶ ሠላሳ ፍልስጤማውያንን ገድሎ ልብሳቸውን ለጓደኞቹ ሰጠ። በእጮኛዋ እና በጓደኞቹ በመታለሉ ተቆጥቶ ፍልስጤምን ትቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳምሶን ወደ ፍልስጤም ወደ እጮኛው ተመለሰ። ጋብቻውን ለማድረግ ዝግጁ በመሆን፣ እሷን ለማግኘት ወደ አባቷ ዘንድ ሄደ። አባቷ ግን ከሳምሶን ጓደኞች ለአንዱ ሚስት አድርጎ ድሯት ነበር። ሳምሶን በአማቱ በጣም ስለተናደደ ሄዶ 300 ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ።ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ።
ሳምሶንን ያነሳሳው በቀል ነበር። ያደረገው ነገር በፍልስጥኤማውያን ልብ ውስጥ ብዙ ቁጣ ቀስቅሶ ስለነበር፤ሊዋጉት ሦስት ሺሕ ሠራዊት ላኩበት። ከዚያም አዲስ የአህያ መንጋጋ ወስዶ፥ ተዋጋቸውም፥ በዚያን ቀን አንድ ሺህ ፍልስጤማውያንን ሰው ገደለ። የእስራኤል ሕዝብ፣የሳምሶንን ታላቅ ጥንካሬ እና ፍልስጤማውያንን ለማሸነፍ ያለውን ፍላጎት ተገንዝበው፣በእነርሱ ላይ አለቃ አድርገው ቀቡት- ሳምሶን ለሃያ ዓመታት በእስራኤል ላይ የሚፈርድበት የስልጣን ወንበር ነው (መሳፍንት 15:20 ተመልከቱ) ።
የእስራኤል መሪ እንደመሆኑ መጠን የሳምሶን የስነ ምግባር ሕይወት ብዙ የሚፈለግ ነበር። በመሣፍንት 16:1 ሳምሶን ሴተኛ አዳሪ አይቶ ወደ ፍልስጤም እንዴት እንደሄደ እና ከእርሷ ጋር እንደተኛ እንመለከታለን። ከፍልስጤማዊው ጋለሞታ ጋር በመተኛት በጠላት ግዛት ውስጥ ሳምሶን ምን እያደረገ እንደነበረ ያስደንቀናል። ይህ በእስራኤል ውስጥ ውርደትን መፍጠር ብቻ ሳይሆን የፍልስጥኤማውያንን ቁጣ ቀስቅሷል። የጋዛ ሰዎች ሳምሶን ወደ ከተማቸው መጥቶ ከአንዲት ዝሙት አዳሪአቸው ጋር መተኛቱን በሰሙ ጊዜ እሱን ለመግደል በማሰብ ቤቱን ከበቡት። ሳምሶን ግን ሳይታወቅ ከከተማዋ አምልጦ ሄደ።
ይህ ብዙም ሳይቆይ ሶምሶን በሶሬቅ ሸለቆ ውስጥ የምትኖር ፍልስጤማዊቷን ሴት ወደደ። ስሟም ደሊላ ይባላል። ከእሷ ጋር ገባ። አሁንም፣የእስራኤሉ አለቃ ለምን በእስራኤል ውስጥ እንደማይኖር፣ነገር ግን ከፍልስጤማዊቷ ሴት ጋር ለመኖር ለምን መረጠ የሚለው ያስደንቀናል። ይህ በእስራኤል ዘንድ ግራ መጋባት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት እንችላለን። ሳምሶን በጠላት ግዛት ውስጥ መገኘቱ ለፍልስጥኤማውያን የጎን እሾህ ነበር። እርሱን ለመግደል ያለማቋረጥ እየሞከሩ ነበር። ይህ ጥቃቶቻቸውን ዘንግቶ የሚመስለው ሳምሶንን የሚረብሽ አይመስልም።
ሆኖም በደሊላ ማታለል ምክንያት ሳምሶን በመጨረሻ እስረኛ ሆነ። የታላቁን ጥንካሬ ምስጢር ከነገራት በኋላ ፀጉሩን ላጨችው ከዚያም ጠላቶቹ እንዲይዙት ጋበዘቻቸው። እነርሱም ዓይኖቹን አወጡት። ሳምሶን እስር ቤት ውስጥ እንደታሰረ፣ የጥንካሬው ምስጢር የነበረው ጸጉሩ ተመልሶ ያድግ ጀመር። ፍልስጥኤማውያን ወደ አምላካቸው ለዳጎን ክብረ በዓል ወቅት እንዲያዝናናቸው ሲወስዱት ሳምሶን ሁሉም ሰው ወደተሰበሰበበት ወደ ታላቁ ቤተ መቅደስ ዓምዶች እንዲመራው አንድን ወጣት ጠየቀ።
በመሣፍንት 16፡28 ሳሞሶን ወደ እግዚአብሔር እንደጮኸ እናባለን፡
28 ሶምሶንም፦ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ። (መሣፍንት 16)
ሳምሶን ወደ እግዚአብሔር የጮኸበት ብቸኛው ጊዜ ይህ ይመስላል። ልብ በሉ፣ እርሱ የጥንካሬው ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑን ያውቃል። ሆኖም፣ ከዚህ ፍላጎት በስተጀርባ ያለው ፍላጎት ዓይኖቹን በማውጣታቸው ምክንያት ጠላቶቹን ለማጥፋት በቀል መፈለጉ ነው። በእነዚህ የመጨረሻዎቹ የሳምሶን ቃላት ውስጥ የእግዚአብሔር ክብር አልተጠቀሰም። ወይም ስለ ሕዝቡ መዳን የሚጨነቅ አይመስልም። የንስሐ ጸሎትም አልጸለየም። ሳምሶን ወደ እግዚአብሔር የጮኸው እሱ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ሳይሆን ለራሱ ነበር።
እግዚአብሔር ያንን ጸሎት መለሰ፤ከዚያም በዳጎን ቤተመቅደስ ውስጥ የነበረውን ሁለት ዓምዶችን ገፍቶ ሳምሶን ሕንፃውን በእሱ እና በዚያ በነበሩት ሁሉ ላይ አፈረሰው። ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ከገደለው በላይ በዚያ ቀን በርካታ ፍልስጤማውያንን ገደለ (መሳፍንት 16፡30) ። ለሳምሶን እናት የተነገረው ትንቢት እውን ሆነ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከፍልስጥኤማውያን ለማዳን ልጇን ተጠቅሟል።
እግዚአብሔር በዚያ ቀን የተጠቀመበትን ሰው ተመልከቱ። ሳምሶን ለጌታ የገባውን ቃል ችላ ያለ ሰው ነበር። ይህም ቃሉን ስለማፍረሱ ብቻ ሳይሆን በማፍረሱም ምክንያት ይቀልድ ነበር። ከባዕዳን ሴቶች ሚስት በመፈለግ የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፏል። እንዲሁም ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ይተኛ ነበር፣ ሚስቱ ካልሆነች ሴት ጋር ይኖር ነበር። ያለ ምንም ጸጸት ወይም ንስሐ ይኖር ነበር። ሳምሶን ሲናደድ በጣም ጨካኝና በበቀል የተሞላ ይሆናል። ስለ እግዚአብሔር ሃሳብ ደንታ የሌለው እና ለራሱ ብቻ የሚያስብ ግለሰብ ነበር። ይህም ጌታን የሚፈታተን በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በሕይወቱ ውስጥ የወሰናቸው ውሳኔዎች ሁሉ ለሕዝቡ ወይም በሕይወቱ ለመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ አክብሮት ያሳየ አልነበረውም።
በስተመጨረሻም በዚህ ሁሉ ክፋት ተያዘ። አብሯቸው የተኛቸው ሴቶች ሁሉ ጠላት ሆኑበት። የፈተዋጋቸው ፍልስጤማውያን ዓይኖቹን አወጡት። የእግዚአብሔርን ሕግ አለማክበሩ ዓይነ ስውር እስረኛ ሆኖ የሕይወቱ ፍጻሜ ሲደርስ ተመልክተናል። እነዚህ ነገሮች ቢኖሩም፣እርሱ ሕዝቡን ከፍልስጥኤማውያን ጭቆና ለማዳን የእግዚአብሔር መሣሪያ ነበር።
እንደ ሳምሶን ያለ መጋቢ ለቤተክርስቲያናችሁ ትቀጥራላችሁን? የእናንተ የወንጌል ተልዕኮ ሥራ መሪ እንዲሆን ትቀበሉታላችሁን? እግዚአብሔር እንዲሰራ በጠራው ሥራ ውስጥ የስኬቱ ምስጢር ምን ነበር? በእርግጥ በኑሮው እግዚአብሔርን የሚፈራ አልነበረም። ወይም በባህሪው ትሑት አልነበረም። ሳምሶን በርካታ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ለአገልግሎቱ ስኬት ብቸኛው ማብራሪያ የሚሆነው እግዚአብሔር ሊጠቀምበት መወሰኑ ብቻ ነው። እግዚአብሔር በበቀል የተሞላውን፣ ራስ ወዳድ የሆነውን እና የማይታዘዘውን ብርቱ ሰው ለሕዝቡ ነጻነትን ለማምጣት ተጠቅሞበታል። ሳምሶን ለእግዚአብሔር ታማኝ አልነበረም ፣ ዳሩ ግን በእርግጥ ዓላማውን ለማሳካት የእግዚአብሔር መሳሪያ ነበር።
ለምልከታ፡
• ሳምሶን በተወለደ ጊዜ እግዚአብሔር ለእርሱ ስላለው ዓላማ ምን እንማራለን? እግዚአብሔር በእርሱ ለመሥራት የሰጠው የተስፋ ቃል ምንድ ነው?
• ሳምሶን ለጌታ የገባውን ቃል ያላከበረው እንዴት ነው?
• ሳምሶን የእግዚአብሔርን ሕግ እንዴት እንደናቀ የሚያሳይ አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጡ።
• ሳምሶን በሕይወቱ ስላለው የእግዚአብሔር ዓላማ ታማኝ ነበርን? ስኬታማስ ነበርን?
• ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን እና በአገልግሎት ፍሬያማነት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ሁለቱ ሁልጊዜ ይዛመዳሉን?
ለጸሎት:
• ጌታ ዓላማውን በእኛ ለመፈጸም ባለመታዘዛችን እና ታማኝ ባለመሆናችን ምክንያት ስለማይገደብ አመስግኑት።
• ለእሱ የበለጠ ታማኝ ትሆኑ ዘንድ ጌታ እንዲረዳችሁ ጠይቁ። በሕይወታችሁ ውስጥ ያለን ማንኛውንም የኃጢአት መንገዶች እንዲገልጥላችሁ ጠይቁት። በጌታም ፊት ተናዘዙ።
• በአገልግሎታችሁ ለመጣው ስኬት ምክንያቱ ችሎታችሁ እና ጥንካሬአችሁ መሆኑን በእውነት ላመናችሁበት ጊዜያት ጌታን ይቅር እንዲላችሁ ጸልዩ። ምንም እንኳን ድክመቶች ቢኖሩብንም በእኛ እና በእኛ ውስጥ ስለሚሠራው ጌታ አመስግኑት።
ምዕራፍ 4 - በሃገር ላይ ተጽዕኖ ያመጣው ታጋዩ አባት
ቢዩ ሳሙኤል በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እና እድገት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ሰው ነበር። ውልደቱ ተአምራዊ ሲሆን ጥሪው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ግልፅ ነበር። የተወለደው ከሕልቃናና ከሚስቱ ሃና ነበር። በተለይ ስለ ልደቱ አስገራሚ የነበረው እናቱ ልጅ መውለድ የምትችል አለመምሰሏ ነው (1ኛ ሳሙኤል 1:2 ተመልከቱ) ።
እንግዲህ ይህ መጸነስ አለመቻል ሃናን በጣም ያሳዝናት ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የወለደችው የሕልቃና ሁለተኛ ሚስት ፍናና ብዙውን ጊዜ ሐናን ታስቆጣት ነበር።
6 እግዚአብሔርም ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር። 7 በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፤ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር። (1 ሳሙኤል 1)
በአንድ ወቅት፣ቤተሰቡ በሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ በነበረበት ወቅት፣ሃና በዚህ ልጅ መውለድ ባለመቻሏ በጥልቅ ጭንቀት ወደ ጌታ ትጸልይ ነበር። በዚያች ቀን እንዲህ ብላ ጸለየች:
10 እርስዋም፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። (1 ሳሙኤል 1)
በዚያ ቀን፣ሃና ከውስጥ በሆነ ጩኸቷ፣ይህንን ልጅ ለጌታ ለመስጠት እና ለመለየት ቃል ገባች። ልጅ ለራሷ የፈለገችውን ያህል፣ይህ ልጅ ሙሉ በሙሉ ለጌታ የተሰጠ ይሆናል አለች።
እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ ወንድ ልጅ ፀነሰች። ለገባችው ስለት ታማኝ በመሆን፣ ጡት እስኪጥል ድረስ ሐና ሃና ዘንድ ቆየ ከዚያም በለጋ ዕድሜው በካህኑ እንክብካቤ ወደሚያድግበት ማደሪያው ድንኳን አመጣችው። ሳሙኤል በካህኑ ኤሊ እየተማረ ያድግ ነበር። ወጣትነቱን በእግዚአብሔር አገልግሎት ውስጥ እያገለገለ ያሳለፈ።
እግዚአብሔር ሳሙኤልን ማናገር የጀመረው በዚያ በሴሎ ነበር። የመጀመሪያ ትንቢታዊ ቃሉ የተናገረው ለሚያሳድገው ሰው - ለካህኑ ለኤሊ ነበር። የኤሊ ልጆች ለጌታ ታማኝ አልነበሩም። እግዚአብሔር ለሳሙኤል የኤሊ እና የልጆቹ በደል ለዘላለም በእነሱ ላይ እንደሚሆን እና ፈጽሞ ይቅር እንደማይባል ነገረው፡
13 ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤቱ ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ። 14 ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ። (1 ሳሙኤል 3)
አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል በክህንነት ላሳለፈው ለኤሊ እነዚህን ቃላት መናገር ለሳሙኤል ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት እንችላለን። 1ኛ ሳሙኤል 3: 19-21 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሳሙኤል ከጌታ ጋር በነበረው ግንኙነት እና በትንቢታዊ ጥሪው እያደገ እንደሄደ ይነግረናል: “ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር” ይላል፡፡ (1ኛ ሳሙኤል 3:19) በእርግጥ፣የሳሙኤል የነቢይነት ዝና በእስራኤል ውስጥ ታውቆ ነበር። (1ኛ ሳሙኤል 3፡20)
የሐሰተኛ አማልክቶቻቸውን አስወግደው እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያገለግሉ ሕዝቡን በሞገተበት በ1ኛ ሳሙኤል 7 ውስጥ የሳሙኤል ተጽዕኖ በጉልህ ታይቷል። (1ኛ ሳሙኤል 7:3-4) በምላሹም ሕዝቡ በምጽጳ ተሰብስቦ በጾም ወደ ጌታ በንስሐ ጮኸ። ንስሐ ለገቡት ሕዝቦቹ የጌታ መገኘት በተገለጠበት ጊዜ የሆነውን ተመለከቱ፡
10 ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጐድጓድ አንጐደጐደ፥ አስደነገጣቸውም፤ በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ። (1ኛ ሳሙኤል 7:10)
ይህ ኃይለኛ የእግዚአብሔር መገለጥ ነበር። በሳሙኤል ዘመን ፍልስጤማውያን እስራኤልን እንደገና አላስጨነቁም፣እንዲሁም በፍልስጤማውያን የተወሰደው የእስራኤል ግዛት ተመልሶላቸዋል (1ኛ ሳሙኤል 7 13-14 ተመልከቱ) ።
ሳሙኤል በየዓመቱ ወደ ቤቴል፣ወደ ጌልጌላ፣ወደ ምጽጳ እየሄደ ከዚያም ወደሚኖርበት ራማ ይመለስ ነበር። እነዚህን የፍርድ ጉዳዮችን ይመለከት ነበር እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል እየተናገረ፣ለሕዝቡ በሕይወታቸው ያለውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እና ዓላማ ይጠቁም ነበር።
የሳሙኤል አገልግሎት ፍሬያማና በኃይል የተሞላ ነበር። ስለ ሳሙኤል አስገራሚ የሆነው ግን የቤተሰቡ ሕይወት ነው። ይህንን በ1ኛ ሳሙኤል 8 አንድ ፍንጭ እናገኛለን፡፡ ሳሙኤል እያረጀ ሲሄድ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው። 1 ሳሙኤል 8፡3 እነዚህን የሳሙኤል ልጆችን እንዴት እንደገለፀ አስተውሉ፡
3 ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር። (1ኛ ሳሙኤል 8)
ሕዝቡ አንድ ቀን ወደ ሳሙኤል መጥቶ እንደ ሌሎቹ ሃገሮች ሁሉ ንጉሥ ያነግስላቸው ዘንድ እንዲጠይቁት እንዳደረጋቸው የተቀመጠ እውነታ ነው።
4 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና፦ 5 እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት። (1ኛ ሳሙኤል 8)
ሕዝቡ ለሳሙኤል ታላቅ አክብሮት ቢኖረውም፣ክፉ ለነበሩት እና ጌታን ላሳደቡት ልጆቹ እንደዚያ ተመሳሳይ ክብር አልነበራቸውም።
እስቲ ይህንን ለአፍታ እናስብ። ሳሙኤል ከጌታ የተነገረው የመጀመሪያው መልዕክት ለአሳዳጊው ለካህኑ ለኤሊ የመጣ መሆኑን አስታውሱ። እግዚአብሔር ኤሊ የክህነት ተግባራቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ ለእግዚአብሔር አክብሮት የሌላቸውን ልጆቹን ባለማስተካከሉ ገሠጸው። የኤሊ ልጆችን ስግብግብ እና ሥነ ምግባር የጎደላቸው በመሆናቸው ገሠጻቸው። እንግዲህ ሳሙኤል ፣ አሁን እራሱን በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ሊያገኘው ችሏል። እንደ ኤሊ ልጆች ሁሉ የሳሙኤል ልጆችም ጉቦ እየተቀበሉ ፍትሕን ያዛቡ ነበር። ሳሙኤል ፈራጆች አድርጎ በመሾም እንደ ኤሊም በቦታቸው እንዲቆዩ አደረጋቸው። ገና በልጅነቱ ለኤሊ በተናገረው ተመሳሳይ ኃጢአት ጥፋተኛ ሊሆን በቃ።
የሳሙኤል ልጆች እስራኤል ከንጉሣቸው ከእግዚአብሔር ፊታቸውን እንዲመለሱ በማድረግ ኃላፊነቱን ይቀበሉ ዘንድ የተገባ ነበር። የሳሙኤል ልጆች ህዝቡን ወደ እግዚአብሔር ከመመለስ ይልቅ፤ሕዝቡ ፊቱን በዙሪያቸው ወደነበሩት ሃገራት እንዲያዞሩ ምክንያት ሆኑ። ሳሙኤል እምነቱን ለልጆቹ ማስተላለፍ አልቻለም። ጌታን የሚያከብሩ ልጆችን ለማሳደግ እንደ አባት ግን ታግሏል።
ሳሙኤል ኃይለኛ ነቢይ ነበር። ከታላላቅ የእስራኤል ነብያት/ዳኞች አንዱ ነበር። የእግዚአብሔርን እውነት በማወጅ እና ለህዝቡ የጌታን መንገድ በማሳየት ብዙ እንደተጓዘ ዳሩ ግን የገዛ ልጆቹ የእርሱን መልዕክት ባለመቀበል በእግዚአብሔር መንገድ እንዳልሄዱ እንመለከታለን። በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያንን ታላቅ እና ኃይለኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ይህ ታጋይ አባት ነበር። ንጉሥ ሳኦል ሳሙኤልን ያከብር ነበር፤ስለሆነም ብዙ ጊዜ ምክርና ተግሳጽን ለመጠየቅ ወደ እርሱ ይመጣ ነበር። ሳሙኤል የምንጊዜም ታላቅ የእስራኤል ንጉሥ በመባል በሚታወቀው ንጉሥ ዳዊት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ነበረው። ዳዊት ንጉሥ እንዲሆን የቀባውም ሳሙኤል ነበር።
ሳሙኤል በየዓመቱ ከከተማ ወደ ከተማ ሲጓዝ በእስራኤል በርካታ ሰዎች ተነክተዋል። ንጉስን ይመክር እና ሕዝቡን በጌታ መንገድ እንዲሄዱ ይሞግታቸው ነበር። የንጉሥ ሳኦል ተተኪ የሆነውን ዳዊትን መምረጡ እስራኤልን ወደ ኃያልነትና የክብር ከፍታዋ አድርሷታል። ምንም እንኳን የገዛ ልጆቹ መንገዱን ባይከተሉም በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነበር።
የሳሙኤል የነቢይነት ስኬት ሚስጥር ምንድ ነበር? ጥበበኛ ውሳኔ ስለወሰደ ነውን? ልጆቹን ዳኞች ለማድረግ የወሰነው ውሳኔ ብዙዎች ከእግዚአብሔር እንዲርቁ አድርጓቸዋል። ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ወጥ የሆነ ጉዞ ነውን? እንደ ኤሊ በተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ መውደቁ፣በዚህ ረገድም እንደወደቀ ያሳያል።
ይህ ታጋይ አባት ግን በነገሥታትና ሃገራት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ምክሩና ተግሳጹ የእስራኤልን ሕዝብ አካሄድ ቀይሯል። የሳሙኤል አገልግሎት ስኬት ከእሱ ብቃት የተነሳ የመጣ ሳይሆን፤እሱን ለመጠቀም በመረጠው በእግዚአብሔር ጸጋ የመጣ ነው። ምናልባት በመላው እስራኤል በመጓዝ የእግዚአብሔርን ቃል ከመስበክ ይልቅ ከቤተሰቡ ጋር ብዙጊዜ ማሳለፍ ይችል ነበር። ልጆቹ መልዕክቱን ባለመቀበላቸው ምክንያት ህመም እንደተሰማው እርግጠኛ ነኝ። የእስራኤል ሕዝብ በዙሪያቸው እንደነበሩት ሕዝቦች ንጉሥን ለመፈለግ ከንጉሣቸው እግዚአብሔር ላይ ፊታቸውን በመመለሳቸው ምክንያት በተወሰነ ደረጃ ኃላፊነት እንደተሰማው እርግጠኛ ነኝ። ምንም እንኳን ውድቀቶች ቢኖሩም፣ የእሱ ተፅዕኖ ለሚመጡት ዓመታት ይቀጥላል። እሱ ሁልጊዜ ጥበበኛ አልነበረም።ምናልባት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ሁልጊዜ መሆን የነበረባቸው አልነበሩም፣ነገር ግን እግዚአብሔር በጸጋው እሱን ለመጠቀም ስለመረጠ ሕይወቱ በኃይል የተሞላ ነበር፡፡
በትግል ውስጥ ባሉ አባቶች እና እናቶች ላይ የእግዚአብሔር ጸጋ ይፈስሳል። እግዚአብሔር ጸጋውን በእኛ ላይ አፍስሶ ፍሬያማና ኃይለኛ አገልግሎት ይሰጠናል ማለት ሁሉንም ነገር በትክክል እናደርጋለን ማለት አይደለም። ውድቀቶቻችን ቢኖሩም እግዚአብሔር ይጠቀምብናል። የሳሙኤል አገልግሎት ምንም እንኳን ውድቀቶች ቢኖሩትም በትግል ውስጥ ባለ ወላጅ ላይ የሚፈሰው ጸጋ ምሳሌ ነው። ግዴታዎቻችንን ችላ እንደማለት አድርገን መውሰድ የለብንም፣ ዳሩ ግን ውድቀቶቻችን ቢኖሩም እግዚአብሔር አሁንም ሊባርከን እንደሚችል እርግጠኛ ሁኑ።
ለምልከታ፡
• እግዚአብሔር ሳሙኤልን የጠራው ገና ሳይወለድ ነበር። የአገልግሎቱ ስኬት የተገኘው ከራሱ እና እንደ ነቢይ ከነበሩት ጥሩ ባሕርያቱ ነው ወይስ ከእግዚአብሔር ጥሪ?
• ሳሙኤል ያደገው በካህኑ ኤሊ ቤት ውስጥ ነው። የኤሊ ልጆች ምን ይመስሉ ነበር? የሳሙኤል ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ትንቢታዊ ቃል ምን ነበር?
• ሳሙኤል እንደ ኤሊ በተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ የወደቀው እንዴት ነው? የሳሙኤል ልጆች ምን ይመስሉ ነበር? የአገልግሎት ሥፍራቸውን ሰጣቸው ማን ነበር?
• ልጆቹ መልዕክቱን ባይቀበሉም የሳሙኤል አገልግሎት ምን ያህል ጉልህ እና ስኬታማ ነበር?
• በአገልግሎት ውስጥ በሚኖር ስኬት እና በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክል መሆን መካከል ያለው ግንኙነት ምንድ ነው? በአገልግሎት ስኬታማ መሆን እና በሌሎች መስኮች መውደቅ ይቻላልን?
• ሳሙኤል ከቤተሰቡ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ይችል ነበር ብላችሁ ታስባላችሁን?
ለጸሎት፡
• ፍጹም ባትሆኑም እንዲሁም ጥፋቶች ቢኖርባችሁም እርሱ ስለሚጠቀምባችሁ ጌታን ያመሰግኑ።
• በቤተሰብ እና በቤተክርስቲያን መካከል ሚዛን መጠበቅ እንድትችሉ ጌታን ጠይቁ። በሕይወታችሁ እና በቤተሰባችሁ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር እግዚአብሔርን ጠይቁ። ለምትወዷቸው ሰዎች ወደ ክርስቶስ አዳኛቸው እንዲመጡ ለመጸለይ ትንሽ ጊዜ ውሰዱ።
• በአገልግሎታችሁ በሚኖር ስኬት ወይም ውድቀት ላይ በመመስረት መንፈሳዊ ሁኔታችሁ ላይ በፍፁም እንዳትፈርዱ ጌታ እንዲረዳችሁ ጸልዩ።
ምዕራፍ 5 - የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚለማመደው እረኛ
ስለ ወጣቱ ዳዊት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው ከ1ኛ ሳሙኤል 16 ነው። እግዚአብሔር የሳኦልን ንግስና ከሻረ በኋላ በሕዝቡ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ሌላ ሰው እንዲቀባ ነቢዩን ሳሙኤልን ላከው። ሳሙኤልም እሴይ ወደሚባል ሰው መኖሪያ ወደ ቤተልሔም ተላከ (1ኛ ሳሙኤል 16:4) ። ሳሙኤል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዳቀረበ፣በዙሪያው የተሰበሰቡትን የእሴይን ልጆች ተመለከተ። ከነዚህ ልጆች አንዳቸውም ንጉስ ይሆኑ ዘንድ የእርሱ ምርጫ እንዳልሆኑ ጌታ ተናገረው። በዚህ ግራ ተጋብቶ ሳሙኤል እሴይን ሌሎች ልጆች እንዳሉት ጠየቀ። እሴይ በመሥዋዕቱ ዘንድ ከቀረቡት ሌላ በጎችን የሚጠብቅ እና የሁሉም ታናሽ የሆነ አንድ ልጅ እንዳለው ነገረው። ከዚያም ወጣቱ ዳዊት በሳሙኤል ፊት ቀርበ፣ጌታም ንጉሥ እንዲሆን ቀባው (1ኛ ሳሙኤል 16:12-13) ። ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ የዳዊት መጀመሪያ ተሞክሮ ነበር።
ሳሙኤል ዳዊትን ሲቀባ የጌታ መንፈስ ከንጉሥ ሳኦል ሸሸ፤ከዚያም በክፉ መንፈስ ይረበሽ ጀመር (1ኛ ሳሙኤል 16፡15 ተመልከቱ) ። እሱን ያረጋጋው የነበረው ሙዚቃ ብቻ ነበር። ይህን የተገነዘበው ንጉሥ ሳኦል በሚጨነቅ ጊዜ ከጎኑ ሆኖ በሙዚቃ ሊያረጋጋው የሚችል ወጣት ሙዚቀኛ እንዲፈልጉ አገልጋዮቹን ላከ። ከአገልጋዮቹ አንዱ ዳዊትን እና የሙዚቃ ችሎታውን ያውቅ ነበር። ስለ ወጣቱም ለሳኦል ነገረው፣ ከዚም ዳዊትም ተጠራ። በእግዚአብሔር ቸርነት ዳዊት ሙዚቃ ለመጫወት ወደ ንጉስ አደባባይ ቀረበ።
በዳዊት እና በሳኦል መካከል ያለው ግንኙነት እያደገ ሄደ ፣ ዳዊትም በሳኦል ፊት ሞገስን አግኘ (1ኛ ሳሙኤል 16:21-22 ይመልከቱ) ። ሳኦልም ዳዊትን ጋሻ ጃግሬው አደረገው። በዚህ ሁሉ ዳዊት ከፊቱ ለሚጠብቀው ተግባር የሚያዘጋጀውን የእግዚአብሔርን በረከት በዳዊት ሕይወት ላይ እንመለከታለን።
በዚያ ዘመን ፍልስጤማውያን ለእስራኤላውያን ችግር ነበሩ። በሁለቱም አገሮች መካከል ጦርነት ይካሄድ ነበር። ከፍልስጤማውያን መካከል ጎልያድ የሚባል ግዙፍ ሰው ነበር። ፍልስጤማውያን ጎልያድን መዋጋት የሚችል አንድ ሰው እንዲልኩ ለእስራኤላውያን ሐሳብ አቀረቡ። ጎልያድን እንዲዋጋ የመረጡት ሰው ቢያሸንፍ ራሳቸውን ለእስራኤል እንደሚያገዙ ተናገሩ። በሌላ በኩል ጎልያድ እስራኤላዊውን ድል ካደረገ፣ከዚያም እስራኤል ሁሉ ለፍልስጤማውያን ተገዥ ይሆናሉ። በእስራኤል ውስጥ ማንም ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቀበል አልደፈረም። ዳዊት ግን እስራኤልን ወክሎ ለመቆም በእግዚአብሔር ተማመነ።
ይህ ወጣት እረኛ በሰይፍ ወይም በጦር አጠቃቀም የተካነ አልነበረም። የእሱ መሣሪያ ቀላል ወንጭፍ ነበር። ሙሉ ትጥቅ ባለው ግዙፍ ሰው ላይ ወንጭፍ ምን ነበር? ልምድ ባለው እና ኃይለኛ ወታደር ላይ እረኛ ምን ነበር?
ጎልያድ ዳዊት ሲመጣ ባየው ጊዜ አሾፈበት። በግልጽ ለመናገር ዳዊት በዚህ ታላቅ ወታደር ላይ ዕድል አልነበረውም። ዳዊት ድካሙን ያውቅ ነበር። በገዛ ኃይሉ እንዲህ ያለውን ግዙፍ ሰው በራሱ ጥንካሬ ለማሸነፍ ምንም ዓይነት አቅም አልነበረውም። በዚያ ቀን ጎልያድን ሲያናግረው እንዲህ አለ:
45 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። 46 እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤47 ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።
ዳዊት “ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው” በማለት ጦርነቱን የሚያሸንፈው ጌታ እንጂ ሰይፍ እና ሰራዊት እንዳልሆነ በዚያ የነበሩትን አስታወሰ። ዳዊት ለዚህ ውጊያ ምስጋናውን ለራሱ አልወሰደም። ጥንካሬው ከጎልያድ ጋር እንደማይመጣጠን ያውቅ ነበር። እሱ በራሱ ምንም የማሸነፍ ዕድል እንደማይኖረው ያውቅ ነበር። ጦርነቱን የሚያሸንፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። በዚያን ቀን ከጸጋ በቀር ሌላ ድል የሚሰጠው አይኖርም። ዳዊት በእግዚአብሔር ስም አንድ ድንጋይ በወንጭፉ ወርውሮ ግዙፉን ሰው ጭንቅላቱ መትቶ ጣለው።
በእግዚአብሔር ጸጋ የሆነው ይህ የእምነት ተግባር ዳዊት በሃገሩ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር የሚረዳውን ስልጣን አመጣለት። ዳዊት በሠራዊቱ ውስጥ ሳኦልን በሚገባ ያገለግል ነበር። እግዚአብሔር ለዳዊት ብዙ ድሎችን ሰጠው። የዳዊት ድሎች ከሳኦል ድሎች ልቀው የሚበልጡ ነበሩ። እንደ እውነቱ ከሆነ በእነዚያ ቀናት አንድ መዝሙር በእነዚህ ቃላት ተዘምሯል፡
7 ሴቶችም፦ ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። (1ኛ ሳሙኤል 18)
ሳኦል በዳዊት በጣም ይቀና ነበር። በእርግጥ ከዚህ ቅናት የተነሳ ብዙጊዜ እሱን ለመግደል ይፈልግ ነበር። ከዚያም ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ተደብቆ ለመኖር ተገደደ። በእነዚያ ከሳኦል ተደብቆ በነበረበት ቀናት ለዳዊት ምን እንደሚመስል አስቡት። ታላቁ ወታደር እና ወታደራዊ አዛዥ ለመሸሽ ተገዷል። ይህ ትሁት አንዲሆን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር በቅጽበት ሊወስድ እንደሚችል ያስታውሰዋል። ዳዊት የእግዚአብሔር ጸጋ ባይጠብቀው ኖሮ በገዛ ንጉሱ እጅ እንደሚጠፋ መገንዘብ ነበረበት። ጎልያድን ቢያሸንፍም እግዚአብሔር ሳኦልን እንዲያሸንፍ አልፈቀደለትም።
ምንም እንኳን ውድቀቶች እና ኃጢአቶች ቢኖሩም በዳዊት ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ጸጋ ማስረጃ ነው። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከሳኦል ሲሸሹ፣ ምግብን ለማግኘት በሌሎች ሰዎች ላይ ጥገኛ ለመሆን ተገድደው ነበር። በአንድ ወቅት ዳዊት ናባል ወደሚባል አንድ ሃብታም ሰው ምግብ እንዲያቀርብለት መልዕክተኞችን ላከ። ናባል ግን ሊረዳው አልፈለገም። በእምቢታው ዳዊትን ሰደበው። ወዲያው ናባልን ለመዋጋት እና በኃይል ያለውን ሁሉ ለመውሰድ ሰዎቹን አዘጋጀ። በዚያ ቀን የዳዊት ቁጣ እጅግ ከመንደዱ የተነሳ እንዲህ አለ፡
22 ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው፥ እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር። (1ኛ ሳሙኤል 25)
የዳዊት ዓላማ በጣም ግልፅ ነው። ናባል የሚያፈልገውን ነገር ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት በናባል ቤት የሚገኘውን ወንድ ሁሉ ሊገድል ነበር። ለዳዊት የእግዚአብሔር ዓላማ ይህ አልነበረም። የናባል ሚስት ከዳዊት ጋር ከተገናኘች እና የሚያስፈልገውን ሁሉ ካመጣችለት በኋላ ዳዊት ዕቅዱን ቢፈጽም የሚሆነውን የኃጢአቱን ከባድነት እና በእጁ ላይ የነበረውን ጥፋተኝነት ተረዳ (1ኛ ሳሙኤል 25፡32-34ን ተመልከቱ) ። ፍጹም እርጋታ የተሞላው እረኛው ዳዊት አንዳንድ ጊዜ ከባድ ውሳኔዎችን በመወሰን ራሱን ችግር ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ሰው ነበር።
ከሳኦል ሞት በኋላ ዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። ከታላላቅ ፍላጎቶቹ አንዱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ለእርሱ ቅርብ እንዲሆን ወደ ኢየሩሳሌም ማምጣት ነበር። ካህናቱ ታቦቱን በአዲስ ሰረገላ አጓጉዘው አምጡ። ይህን በማድረግ ታቦቱ የሚሸከመው በካህናት ብቻ ነው የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ ተላለፉ። ሲጓዙም በሬዎች ይፋንኑ ነበር ከዚያም ታቦቱ ከሠረገላው ላይ የመውደቅ አደጋ አጋጠመው። ዖዛ የሚባል ሰው፣መሬት ላይ እንዳይወድቅ እጁን ዘረጋ። ታቦቱን በዳሰሰበት ቅጽበት ግን የጌታ ቁጣ ነደደ ከዚያም እግዚአብሔር ቀሰፈው ዖዛም ሞተ።
2ኛ ሳሙኤል 6:9-10 ዳዊት እግዚአብሔርን በጣም ስለፈራ ታቦቱ ይዞ የሚቀረውን መንገድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆነም። 2ኛ ሳሙኤል 6:8 ዳዊት ዖዛን በመግደሉ በእግዚአብሔር ላይ እንደተቆጣ ይነግረናል።
8 እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ። (2ኛ ሳሙኤል 6)
በቁጣ ምክንያት ዳዊት ለሦስት ወራት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆነም ነበር። ቁጣው ሲበርድና ዳዊት ታቦቱ ያረፈበት አከባቢ እንዴት እንደተባረከ ባየ ጊዜ ታቦቱን ወደ ከተማ ለማስገባት ያቀደውን ዕቅድ ለመፈጸም ወሰነ። ታቦቱ ወደ ከተማዋ እንደደረሰ ዳዊት በደስታ በፊቱ ይጨፍር ነበር።
የሳኦል ልጅ የሆነችው የዳዊት ሚስት ሜልኮል ዳዊት በታቦቱ ፊት ሲጨፍር አይታ ናቀችው። ይህን ጉዳይ ለዳዊት በነገረችው ጊዜ በ 2ኛ ሳሙኤል 6:22 ላይ እንዲህ ሲል ይመልሳል፡
22 አሁንም ከሆንሁት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፥ በዓይንሽም እዋረዳለሁ፤ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ አላት። (2ኛ ሳሙኤል 6)
ስለዚሀ ሁኔታ ሲናገር አዳም ክላርክ እንዲህ ይላል፡
ከዚያም እንዲህ ይላል፤ሚልኮል እስክትሞት ድረስ ልጅ አልወለደችም፤ምናልባት ዳዊት ከእርሷ ጋር መሆንን አቁሞ፤ወይም እግዚአብሔር በጥበቡ በፍሊስጤማውያን ዘንድ እንደ መጥፎ ዕድል እና ስድብ የሚቆጠረውን መካንነት አምጥቶባትም ይሆናል፡፡ (“Commentary on the Bible by Adam Clarke” Marion, IA: Laridian, 2013 Electronic edition copyright © 2015 by Laridian, Inc., Marion, Iowa. All rights reserved.)
በዚህ በሚልኮል ክስ ምክንያት ዳዊት ከእንግዲህ ከባለቤቱ ጋር አይተኛ ይሆን? በመካከላቸው ያለው ይህ ክርክር ይህንን የትዳራቸውን ገጽታ እንዲያበቃ አድርጎት ይሆን? እንደዚያ ከሆነ ፣ ዳዊት በቁጣ እና ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ባለመሆን ትግል ውስጥ መግባቱን እንደገና ማየት እንችላለን። ይህ በማንኛውም ግንኙነት ውስጥ ከባድ ጉዳይ ነውና።
ከሚስቱ ጋር ይህ ጉዳይ ቢኖርም፣እግዚአብሔር ዳዊትን መባረኩን ቀጠለ። በእነዚህ የሕይወቱ ክፍሎች ዘንድ ታማኝነት የጎደለው ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ዳዊትን ሲጠቀምበት እናያለን። ዳዊት ብዙ የእስራኤል ጠላቶችን ድል በማድረግ በጦርነት በጣም ስኬታማ ሆነ። በእውነቱ፣በጦር ሜዳ የነበረው ስኬት በጣም ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ እሱ ራሱ ወደ ውጊያው የመሄድ አስፈላጊነት እንኳን አይሰማውም ነበር ፣ በቀላሉ ወታደራዊ አዛዦቹን ይልከ ነበር። በአንድ ወቅት ፣ ወታደሮቹ በሰልፍ ላይ ሳሉ፣ዳዊት ቤት ነበር። ከሰዓት በኋላ ዳዊት ከአልጋው ተነስቶ በሰገነቱ አናት ላይ ሲራመድ አንዲት ሴት ከታች ስትታጠብ ተመለከተ። በዚህች ሴት ተማርኮ ስለ ማንነቷ ጠየቃት። ከዚያም ዳዊት ወደ ቤቱ ጋብዞ አብሯት ተኛ። እርሷም ለእርሱ ሲዋጋ ከነበረው ከዳዊት ወታደሮች የአንዱ ሚስት ነበረች። ቤርሳቤህ በዚህ ገጠመኝ ምክንያት ጸነሰች። የእርግዝናዋ ዜና ለዳዊት በደረሰ ጊዜ የጦር አዛዡን ባሏ ኦሪዮን በጦር ሜዳ በሚሞትበት የፊት መስመር ላይ እንዲቆመው አዘዘ። ከዚያም ቤርሳቤህ የገዛ ሚስቱ እንድትሆን ወሰዳት። ዳዊት ይህን ሲያደርግ በዝሙት ብቻ ሳይሆን በነፍስ ግድያም ጥፋተኛ ነበር። ምናልባትም፣ከሚልኮል ጋር የነበረው ግንኙነት እንደነበረው ቢሆን ኖሮ ይህ ክስተት ላይሆን ይችል ነበር።
ፍጹም በእርጋታ የተሞላው እረኛ እና ዘማሪው ዳዊት ናባል ምግብን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት መላውን ቤተሰብ ለመግደል እስከሚዘጋጅ ድረስ በጣም መበሳጨት ብቻ ሳይሆን የሰውን ሚስት ለመውሰድ ሰውን እስከ መግደል የሚደርስ ነው። ዳዊት ለዚህ ኃጢአት ዋጋ ይከፍላል። የዚህ የሐጢአት ግንኙነት ውጤት የሆነው ልጅ ሞተ። ሆኖም ዳዊት ከዚህ ኃጢአት ተጸጽቶ ንስሃ ገባ፣ ከዚያም አስደናቂውን የይቅርታ ጸጋን ሲቀበል ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት ታደሰ። ከዚህ ኃጢአት በኋላ እንኳን እግዚአብሔር በዳዊት ላይ ተስፋ አልቆረጠም። እስራኤልን ወደ ኃይሏና ክብሯ ከፍታ ለማምጣት እሱን መጠቀሙን ቀጥሏል።
ዳዊት በቤተሰቡ ሕይወት ውስጥ ትግል ነበረበት። ልጁ አምኖን እህቱን ትዕማርን ደፈራት (2ኛ ሳሙኤል 13ን ተመልከቱ) ። የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ወንድሙን አምኖንን በትማር ላይ ባደረገው ነገር ምክንያት ገደለው (2ኛ ሳሙኤል 13:23-29 ተመልከቱ) ። በወንድሙ ላይ በሠራው ወንጀል ምክንያት አቤሴሎም ከኢየሩሳሌም ከተማ ለመሸሽ ተገደደ። ለሦስት ዓመታት ዳዊት ልጁን አቤሴሎምን አላየውም (2ኛ ሳሙኤል 13:38-39) ። ዳዊት በኢዮአብ ልመና አማካኝነት ከሦስት ዓመታት በኋላ አቤሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለስ ፈቀደ። ይሁን እንጂ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲቆይ አልፎ ተርፎም ወደ እሱ እንዲመጣ አልፈቀደለትም።
23 ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፥ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ መጣ። 24 ንጉሡም፦ ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ሄደ፥ የንጉሡንም ፊት አላየም። (2ኛ ሳሙኤል 14)
ዳዊት እንደ አባት ልጁን ለማየት አልፈቀደም ወይም ወደ እሱ እንዲመጣ እንኳን ፍቃደኛ አልነበረም። አቤሴሎም ከዳዊት ጋር በአንድ ከተማ ውስጥ ቢኖርም ነገር ግን ከእሱ ጋር ባለው ሕብረት ደስተኛ አልነበረም። ከእሱ ጋር ቁጭ ብሎ ለመነጋገር እና ከአባቱ ጋር ማዕድ መቅረብ በፍጹም አይችልም ነበር። በተመሳሳይ አባቱም ከእሱ ጋር ለመነጋገር ወይም በአንድ ቤት ውስጥ ለመሆን ፈቃደኛ አልሆነም። ይህ በአቤሴሎም ላይ ምን ያህል ሥቃይ እንደሚያደርስ መገመት እንችላለን። እንደ አባት፣ዳዊት ልጁን ይቅር ለማለት ተቸግሮ ነበር። በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው ተለያይተው ይኖራሉ። ከዚያም አቤሴሎም አባቱ እርሱን ባለመቀበሉ ምክንያት ጥላቻ እያደረበት መጣ።
አቤሴሎም ለአባቱ ለዳዊት ባለው ጥላቻ ምክንያት በመንግሥቱ ውስጥ ባሉ ሰዎች ዘንድ እንደ አባቱ ትኩረት ማግኘት ጀመረ። ይህ ውሎ አድሮ አቤሴሎም ራሱን የአባቱ ተቀናቃኝ በመሆን ራሱን ንጉሥ አድርጎ ወደማወጅ መራው። ዳዊት ከአቤሴሎም ጋር ከመዋጋት ይልቅ ቤተሰቡን ይዞ ከኢየሩሳሌም ለመሸሽ ተገደደ። እሱ በሌለበት ቤተሰቡን ይንከባከቡ ዘንድ ቁባቶቹን ትቷቸው ሄደ። አቤሴሎም በንቀት ተነሳስቶ፤በቤተ መንግሥቱ ጣሪያ ላይ ድንኳን ተከለ እዚያም በሕዝቡ ፊት ከአባቱ ቁባቶች ጋር ይተኛ ነበር። ይህ ለአባቱ ያሳየው እጅግ አክብሮት የጎደለው ድርጊት ሲሆን አቤሴሎም አባቱን ምን ያህል እንደጠላው ለሕዝቡ አሳይቷል። አቤሴሎም ለዳዊት የነበረው ጥላቻ ዳዊት እርሱን ለማየት ወይም በእርሱ ፊት ለመገኘት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።
ዳዊት ለኃጢአቱ የሚከፈለው ዋጋ ነበር። ዝሙት የፈጸመው ሰው የገዛ ልጁን በልጁ ተደፍራ ተመለከተ። ሌላኛው ልጁ ከቁባቶቹ ጋር በአደባባይ ለመተኛት በቃ። የወታደሩን ኦሪዮንን ሚስት ለመውሰድ ሲል ነፍስ ያጠፋው ዳዊት፣አንዱ ልጁ ሌላውን ሲገድል ተመልክቷል። እንዲሁም ከቤርሳቤህ ጋር ባደረገው የዝሙት ግንኙነት የተወለደው ሕፃን ሞተ። የኢየሩሳሌምን ከተማ አሸንፎ የገዛው ሰው፣ የገዛ ልጁ ስልጣኑን ከእርሱ ሊወስድ በሚያስፈራራው ጊዜ ከእሱ ለመሸሽ ተገደደ። እነዚህ ሁሉ ለዳዊት ጥልቅ ሥቃይ እና የኃጢአቱ ዋጋ ከባድ ሸክም ነበሩ።
ዳዊት ፍጹም አልነበረም። መላ ቤተሰብን ለማጥፋት የሚያስፈራራ የቁጣ ፍንዳታ ነው። እርሱ በወሲባዊ ኃጢአቶች እና ግድያ ጥፋተኛ ነበር። ዳዊት መሆን የነበረበት አባት አልነበረም በዚህም ምክንያት ልጁ አቤሴሎም ጠላው። ሜልኮል ከእርሱ ጋር በሃሳብ ባልተስማማች ጊዜ የሚተዋት ባል መሆን አልነበረበትም። አንዳንድ ጊዜ የበደሉትን ይቅር ማለት የሚችል ሰው አልነበረም። የዳዊት መዝሙሮችን ፈጠን ብለን ብናነብ ዳዊት አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕይወቱ ያለውን ዓላማ ለመግለጽ ይታገል እንደነበር ያስተምረናል። ዳዊት የራሱ ችግሮች ነበሩበት። እነዚህ ሐጢአቶች በዘመናችን ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በርካቶች መጋቢ እንዳይሆኑ ይከለክላሉ።
እግዚአብሔር ግን ዳዊትን አልተወውም። በሚያስደንቅ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ጸጋ ይለማመድ ነበር። በጎልያድ ላይ ድልን የሰጠው አምላክ በንግስና ዘመኑ ሁሉ ከእርሱ ጋር አብሮት ነበር። ዳዊት በወደቀ ጊዜ እንኳን የእግዚአብሔርን ምሕረት ያውቅ ነበር። የዳዊት የንግስና ዘመን የስኬት ሚስጥር ምን ነበር? የእሱ የሞራል ታማኝነት ነበርን? ቤተሰቡን ያሳደገበት መንገድ ነበርን? ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በመከተሉ ነበርን? በእነዚህ ሁሉ የሕይወቱ ክፍሎች ዳዊት እንደወደቀ እናውቃለን። እግዚአብሔር ግን ለዚህ ሰው ዓላማ ነበረው። የእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ እረኛ በነበረው የአሁኑ ንጉሥ ላይ ከስህተቶቹ ሁሉ ጋር ነበር። እግዚአብሔር በእርሱ ተስፋ አልቆረጠም። ዳዊት ሕይወቱንና ንግሥናውን ሲመለከት ፣ በሁለት ጉዳዮች ውስጥ ያለ ይመስለኛል። መጀመሪያ ፣እግዚአብሔርን ብዙ ተጠራጥሯል እንዲሁም ወድቋል። ሁለተኛ፣ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል።
ለምልከታ፡
• ሳሙኤል አዲስ የእስራኤልን ንጉሥ ሊቀባ በመጣ ጊዜ ዳዊት የት ነበር? በሳሙኤል መሥዋዕት ላይ አለመገኘቱ ቤተሰቦቹ እርሱን የሚመለከቱበት መንገድ ምን ያስተምረናል?
• ዳዊት ጎልያድን በመግደሉ ምክንያት ድሉን ራሱ እንዳመጣው አድርጎ ቆጥሮታልን? እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በሚያደርገው ነገር ምስጋናውን ለመቀበል ለምን አሰብን? ምስጋናው እንደሚገባን እስከምን ድረስ ይመስለናል?
• ስለ ዳዊት ቁጣ ምን እንማራለን? ንዴቱ መላ ቤተሰብን ያጠፋል ማለት ምን ማለት ነው?
• ስለ ዳዊት የቤተሰብ ሕይወት ምን እንማራለን? ከሚስቱ ሚልኮል እና ከልጁ ከአቤሴሎም ጋር የነበረውን ግንኙነት ግለጹ።
• የዳዊትን የንግስና ዘመን ስኬት እንዴት ትገልጹታላችሁ? ይህ ስኬት በዳዊት ላይ የተደገፈው እስከ ምን ድረስ ነው? በእግዚአብሔር ላይ የተመካው እስከ ምን ድረስ ነው?
ለጸሎት፡
• ደካማ በሆኑ ሰዎች ውስጥ እንኳን ለመስራት ጸጋው ያለውን አቅም ለማየት እንዲረዳችሁ ጌታን ጠይቁ።
• በእናንተ ውስጥ ለሚሠራው ሥራ ክብር ለመስጠት ፈቃደኛ እንድትሆኑ ጌታ እንዲረዳችሁ ጠይቁ። እኛ ባይገባንም እንኳን እርሱ አሁንም እኛን እና አገልግሎታችንን እየባረከ በመሆኑ አመስግኑት።
• በቤተሰባችሁ ግንኙነቶች ውስጥ እንዲመራችሁ ጌታን ጠይቁ። ከሚስት ወይም ከባል እና ከልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት እንደ አስፈላጊ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አድርጋችሁ እንድትመለከቱ እግዚአብሔር እንዲረዳችሁ ጠይቁ።
ምዕራፍ 6 – በነብያት ደካም የሚገለጠው የእግዚአብሔር ኃይል
በእስራኤል ካሉ የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ፤ነቢያት እጅግ የተከበሩ እንዲሁም የተጠሉ ነበሩ። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ ወሳኝ አካል ነበሩ፣ሃሳቡን እና ዓላማውን ለሕዝቡ ያስተዋውቁ ነበር። ነቢያት ሆነው እንዲያገለግሉ በእግዚአብሔር የተጠሩትን አራት ሰዎች ሕይወት በአጭሩ መመልከት እፈልጋለሁ
አሞጽ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሞጽ የሚናገረው ትንሽ ነው። እሱ ከቤተልሔም በ 19 ኪሎ ሜትር (12 ማይል) ርቀት ላይ በምትገኘው በቴኮአ ክልል ውስጥ ይኖር እንደነበር እናውቃለን። እግዚአብሔር እንዲሰብከው የፈለገው መልእክት በተለይ በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። በወቅቱ የነበረው ካህን አሜስያስ የሚባል ሰው ነበር። የአሞጽን መልዕክት ሰምቶ ገሠጾ በከተማው ውስጥ ዳግመኛ እንዳይናገር ከለከለው።
12 አሜስያስም አሞጽን፦ ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥13 በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው። (አሞጽ 7)
አሞጽ ለካህኑ ለአሜስያስ ግሳጼ ምላ እንዲሆን ራሱን እንዴት እንደገለጸ አስተውሉ፡
14 አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው፦ እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤15 እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። (አሞጽ 7)
አሞጽ መቼም እንደ ነቢይ ሥልጠና አላገኘም። በነብይ ቤትም አላደገም። የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ የመሆን ብቃቶች ባይኖሩትም በሕይወቱ የእግዚአብሔር ጥሪ ግን ነበረው። የተናገረውም በዚህ መሠረት ብቻ ነበር።
አሞጽ አገልግሎቱ ውስጥ ለነበረው ስኬት ቁልፉ ምንድ ነው? ባገኘው ሥልጠና ወይም ተሞክሮው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጥሪ የመጣ ነበር። ያለዚህ ጥሪ፣አሞጽ እረኛ ብቻ ነበር። በሕይወቱ የእግዚአብሔር ቅባት ባይኖር፣አሞጽ አገልግሎት አይኖረውም ነበር። ለዚህ አገልግሎት ለጠራው የእግዚአብሔር ጸጋ ዕዳ ነበረበት።
ሆሴዕ
ሆሴዕ ብዙም የማናውቀው ሌላ ነቢይ ነው። እግዚአብሔር ጎሜር የተባለችውን የዲብላይምን ሴት ልጅ እንዲያገባ ጠየቀው። ሆኖም ጎሜር ከተጋቡ በኋላ ለእርሱ ታማኝ አልነበረችም ነበር። ሚስቱን ዳግም እንዲወዳት እግዚአብሔር ነቢዩን እንዴት እንደተናገረው በሆሴዕ 3 እናነባለን። ይህንን ለማድረግ ሆሴዕ ከሌላ ሰው መልሶ ሊገዛት የተገባ ነበር።
በብዙ ጉዳዮች ሆሴዕ በጌታ ስም ይሰብክ ዘንድ ብቁ እንዳይሆን ይህ ምክንያት ይሆን ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ የሙሴ ሕግ ካህኑ ከጋለሞታ ወይም ከረከሰች ሴት ጋር መጋባት እንደሌለበት ይገልጻል።
7 ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፈታችውን አያግባ። (ዘሌዋውያን 21)
ተመሳሳይ ሕጎች በእግዚአብሔር ነቢይ ላይ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። እግዚአብሔር ግን ከሕዝቡ ጋር የነበረውን ግንኙነት በምሳሌ ለማስረዳት የሆሴዕና የጎሜርን ጋብቻ ተጠቅሟል። ጎሜር ለባሏ ታማኝ እንዳልሆነች ሁሉ የእግዚአብሔር ሰዎችም ለእርሱ ታማኝ አልነበሩም። እግዚአብሔርም ሕዝቡን መውደዱን አላቆመም። እንደ እውነቱ ከሆነ እሱ መልሶ ሕዝቡን የሚገዛበትን ወይም የእርሱ የሆኑትን የሚዋጅበትን መንገድ ያዘጋጃል።
በዚህ አውድ ውስጥ ስለ ሆሴዕ የምናገረው ለምንድ ነው? ይህን የምናገረው ለትዳሩ በጥልቅ መታገሉን የሚያሳይ ስለሆነ ነው። ሚስቱ ታማኝ ያልሆነች እና ለሚያገለግላቸው ሰዎች መጥፎ ምሳሌ በመሆኗ ምክንያት ነው። ሰዎቹ ስለ ሆሴዕ እና ስለ ባለቤቱ ጎሜር ሲናገሩ መስማት ትችላላችሁ። በትዳራቸው እየሆነ ስላለው ነገር አላዋቂ ባልሆኑ ነበር። የሆሴዕ አገልግሎት ስኬታማ የነበረው በትዳሩ በገጠመው ችግር ሳይሆን በሕይወቱ ባለው የእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር የፈረሰውን ጋብቻ ዓላማውን ለማሳካት መረጠ።
ዕንባቆም
ዕንባቆም በእግዚአብሔር ወደ አገልግሎት የተጠራ በአንጻራዊ ሁኔታ የማይታወቅ ነቢይ ነው። ይህ ሰው ለእርዳታ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዳልሰማው ተሰማው። የትንቢቱን የመክፈቻ የሆኑትን መልዕክት አዳምጡ፡
2 አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም። (ዕንባቆም 1)
በዚህ ዓለም ስላለው ክፋት ምንም ባለማደረጉ እግዚአብሔርን መክሰሱን ይቀጥላል፡
3 በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ። (ዕንባቆም 1)
በእነዚህ የመክፈቻ ጥቅሶች ውስጥ ዕንባቆም ያቀረበው ሥዕል የሕዝቡን ጩኸት የማይሰማ እና ስለ ኢፍትሃዊነት ምንም ለማድረግ የማይመርጥ አምላክ የሚል ነው።
እነዚህ ሁላችንም የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ቢሆኑም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ፣እግዚአብሔር ወደ ትንቢታዊ አገልግሎት የጠራቸው ከዚህ የበለጠ ለእግዚአብሔር ከፍ ያለ አመለካከት ይኖራቸዋል ብለን እንጠብቃለን። በዕንባቆም መጽሐፍ ውስጥ ጌታ እነዚህን ጥያቄዎች ይዳስሳል ፣ ስለዚህም ነቢዩ በመጨረሻ ጻድቅ ነገሮች በመልካም ሁኔታ በማይሄዱበት እና የእግዚአብሔር መንገዶች ባልገባንም ጊዜ እንኳን በእምነት መኖር እንደሚገባው ተረድቷል (ዕንባቆም 2:4፤ 3:17-18 ተመልከቱ) ።
የዕንባቆም መጽሐፍ የእግዚአብሔርን መንገድ እና ዓላማ ለመረዳት የነቢዩን ተጋድሎ የሚገልጽ ነው። ዕንባቆም ስለ እግዚአብሔር መንገድ ለሚጠይቁት መልስ የለውም። እሱ ማድረግ የሚችለው ሰዎች በዙሪያቸው ምን እየተከናወነ እንደሆነ ባይረዱም እንኳን በእግዚአብሔር ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማሳሰብ ነው።
እግዚአብሔር ዕንባቆምን ለምን መረጠ? ጠንካራ የሆነ ሥነ-መለኮታዊ ግንዛቤ ስላለው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣እግዚአብሔር በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች ለማናገር ድክመቱን እና የእውቀት ጉድለቱን ተጠቅሞበታል።
ዮናስ
በመጨረሻም፣ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ሁሉ በጣም ዝነኛ የሆነውን አንዱን ለመመልት ትንሽ ጊዜ መውሰድ እፈልጋለሁ። ዮናስ የእግዚአብሔርን ቃል መናገር የማይፈልግ ነቢይ በመባል ይታወቃል። እግዚአብሔር በዚያች ከተማ ሕዝብ ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ያስጠነቅቃቸው ዘንድ ወደ ነነዌ እንዲሄድ ዮናስን በጠራው ጊዜ ዮናስ ፈቃደኛ አልነበረም። በእርግጥ ፣ ከእግዚአብሔር ለማምለጥ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ለሚሄድ መርከብ ላይ ተሳፈረ። (ዮናስ 1:1-3ን ተመልከቱ)
እግዚአብሔር ዮናስ እንዲሄድ አልፈቀደለትም። መርከቧን የሚሰብር የሚመስል ኃይለኛ ነፋስን በመላክ፤እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ። መርከበኞቹ ሕይወታቸውን እንዳያጡ በመፍራት በመርከቡ ላይ የጫኑትን ጭነቶቻቸውን በመጣል ወደ አማልክቶቻቸው እንዲያድናቸው ይጮኹ ነበር። ዮናስ ግን በመርከቡ ታችኛው ክፍል ውስጥ ተኝቶ ነበር፡፡
ለአውሎ ነፋሱ ተጠያቂው ማን እንደሆነ ለማወቅ መርከበኞቹ ዕጣ ተጣጣሉ። ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ። ያደረገውን እንዲናዘዝም ተገደደ፣ዮናስም እውነቱን ነገራቸው። አውሎ ነፋሱ ጸጥ ይል ዘንድ ወደ ባህሩ እንዲወረውሩት ነገራቸው። ዮናስ ወደ ባሕሩ በተወረወረ ጊዜ ማዕበሉ ልክ እንደተናገረው ቆመ። ይህ በእነዚያ አግዚአብሔርን የማያውቁ መርከበኞች ላይ እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖ አሳድሮ በዚያው መርከብ ላይ ለዮናስ አምላክ ለጌታ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ተጽዕኖ አደረገባቸው (ዮናስ 1፡16ን ተመልከቱ) ። በዮናስ አለመታዘዝ ምንያት የእነዚህ መርከበኞች ዓይኖች ለእስራኤል አምላክ ተከፈተ።
እግዚአብሔር ዮናስን በዋጠውና በባሕሩ ዳር ላይ በተፋው በትልቁ ዓሳ አማካኝነት ከኃለኛው ባሕር አዳነው። ከዚያም እግዚአብሔር ዮናስን ወደ ነነዌ ሄዶ መልዕክቱን እዚያ ላሉት ሰዎች እንዲያደርስ ነገረው። በዚህ ጊዜ ዮናስ ታዘዘ። ዮናስ ጌታን ቢታዘዝም፣ለሕዝቡ ያለው ልብ እንዳልተለወጠ ግን መረዳት አስፈላጊ ነው። ዮናስ ወደ ነነዌ ሄዶ የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ላይ ሊመጣ እንደሆነ ለሕዝቡ ነገራቸው። በዚህ መልዕክት በጣም ተነክተው ስለነበር ከኃጢአታቸው ተጸጽተው እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው ጮኹ። እግዚአብሔርም ይቅር ብሏቸው በነነዌ ላይ ሊመጣ ያውን ፍርድ ሻረው።
ለእግዚአብሔር ምህረት የዮናስ ምላሽ ምን እንደነበር አስተውሉ፡
1 ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፥ እርሱም ተቈጣ። 2 ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና፦ አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር። 3 አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው። (ዮናስ 4:1-3)
እነዚህ የዮናስ ቃላት ለነነዌ ሰዎች ያለውን አመለካከት ያሳያሉ። ሕዝቡን ስለማይወዳቸው በሐጢአታቸው ምክንያት ሲጠፉ ማየት ይፈልግ ነበር። እግዚአብሔር በዮናስ መልዕክት አማካኝነት ሕዝቡን በንስሐ ይቅር እንደሚላቸው ስላመነ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሲልከው ወደ ነነዌ ለመሄድ ፈቃደኛ አልነበረም። ዮናስ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው ሳይሆን እንዲኮንናቸው ፈልጎ ነበርና። እንደ እውነቱ ከሆነ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር ካላቸው ዮናስ በሕይወት ለመኖር አልፈለገም ነበር።
እግዚአብሔር የዮናስን አገልግሎት በማይታመን ሁኔታ ተጠቅሞበታል። በመርከቡ ውስጥ የነበሩ መርከበኞች የእስራኤልን አምላክ ለማምለክ ሰገዱ። በነነዌ ከተማ የሚኖር ህዝብ ሁሉ በመልዕክቱ ልቡ ተሰብሮ ለሰሩት ከኃጢአት ንስሃ ገቡ። የዮናስ መልዕክት ከአመጸኛ እና ከማይታዘዝ ልብ የመጣ ነው። የእግዚአብሔርን ፍርድ መጥቶ እነዚህን ሰዎች እንዲጠፉ ቢናፍቅም ዳሩ ግን ለሚጠላው ህዝብ ሰበከ። ለመስበክ ታዛዥ ቢሆንም ልቡ አሁንም በአመፅ ውስጥ ነበር። የነነዌን ሕዝብ ይቅር በማለቱ በእግዚአብሔር ላይ ተቆጣ።
የዮናስን አገልግሎት ይህን ያህል ኃይለኛ ያደረገው ምንድን ነው? ለነነዌ ሰዎች ወይም በመርከቡ ውስጥ ለነበሩ መርከበኞች የነበረው መልካም አመለካከት እና ሸክም አልነበረም። ለእነዚህ ሰዎች ስለጸለየም አልነበረም። ለነነዌ ሰዎች በጥላቻ እና በምሬት የተሞላውን ቃል ስለ ሰበከ አልነበረም። ለዮናስ አገልግሎት ኃይለኛ ስኬት ብቸኛው ማብራሪያ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ዓመፀኛ እና መራራ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ተጠቀመበት። የዮናስ ስኬት ከእሱ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም–ሁሉም ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኘ ነበር፤ስለሆነም ዮናስ ፈቃደኛ ባይሆንም ከእርሱ ጋር መስራትን መረጠ።
ከእነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች ምን እንማራለን? አሞጽ ምንም የተማረው ትምህርት አልነበረውም። ሆሴዕ ደግሞ አመንዝራ የሆነች ሚስት አግብቶ ነበር። ዕንባቆም ምንም መልስ አልነበረውም። ዮናስ በአመፅ እና ባለመታዘዝ ይኖር ነበር። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ግን ዓላማዎቹን ለመፈጸም እግዚአብሔር በኃይል ተጠቅሞባቸዋል። የስኬታቸው ምክንያት ከእነርሱ የመጣ ሳይሆን ዳሩ ግን ድክመቶቻቸውን ለስሙ ክብር ለመጠቀም ከመረጠው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ለመጠቀም የሚመርጠው ድካማችንን ቢሆንም ዳሩ ግን ጥንካሬአችንን እና ያለነን ተሰጥዖ ለመጠቀም አይከለከልም፡፡
27 ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ (1ኛ ቆሮንቶስ 1)
ለምልከታ፡
• ነቢዩ አሞጽን ነብይ ይሆን ዘንድ ብቁ ያደረገው ምንድ ነው?
• የሆሴዕና የሚስቱን ጋብቻ ግለጹ። እግዚአብሔር የፈረሰውን ትዳራቸውን ተጠቅሞ ለእስራኤልን ሕዝብ መልዕክቱን ለማስተላለፍ እንዴት ተጠቀመ?
• ዕንባቆም በመጽሐፉ መክፈቻ ምዕራፍ ላይ እግዚአብሔርን የከሰሰበት ምክንያት ምንድን ነው?
• ዮናስ እግዚአብሔር ለጠራቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?
• እግዚአብሔር የእነዚህን ሰዎች ድክመቶች ለክብሩ የተጠቀመው እንዴት ነው?
• እግዚአብሔር ድክመቶቻችንን መጠቀም ከቻለ በጥንካሬያችን የምንመካበት ምክንያት ምንድ ነው?
ለጸሎት፡
• ድክመቶታችሁን ለመለየት ትንሽ ጊዜ ውሰዱ። በእርሱ ፊት አኑሯቸው ከዚያም እግዚአብሔር እንዲያበረታችሁ ወይም ድካማችሁን ለክብሩ እንዲጠቀምበት ጸልዩ፡፡
• በድካሞቻችሁ እንዲጠብቃችሁ ጌታን ጠይቁ። ትዳራችሁን እና የቤተሰብ ግንኙነታችሁን እንዲያጠናክር እና ተገቢ ያልሆነ አመለካከታችሁን እንዲፈውስ ጸልዩ።
• በብርታታችሁ ስላላችሁ ኩራት ወይም መታበይ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላችሁ ጸልዩ፡፡ ደካሞች ስንሆን እንኳን እኛን ስለሚጠቀምብን አመስግኑት።
ምዕራፍ 7 - የባዕድ ሃገር ነገስታት እና የእግዚአብሔር ዓላማ
ብዙጊዜ በአገልግሎት ውስጥ የሚኖር ስኬት ለጌታ ካለን ታማኝነት የተነሳ እንደሆነ ይሰማናል። የተሳካ አገልግሎት ያላቸው ሰዎችን ስንመለከት ከጌታ ጋር በጣም ቅርብ በመሆናቸው ምክንያት እንደተሳካላቸው እናስባለን። ነገር ግን ይህ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ አይደለም። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሦስት የባዕዳን ነገሥታትን ሕይወት እና እግዚአብሔር ዓላማውን በእስራኤል ለማሳካት እንዴት እንደተጠቀመባቸው መመልከት እፈልጋለሁ።
ፈርኦን እና የእግዚአብሔር ታዕምራት መገለጥ
መመልከት የምፈልገው የመጀመሪያው ንጉሥ በሙሴ እና በእስራኤል ባርነት ዘመን የነበረውን የግብፅ ንጉስ ፈርዖንን ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከዮሴፍ ዘመን ጀምሮ በግብፅ ይኖር ነበር። ነገር ግን ስኬታቸው ፈርዖን በጭካኔ እንዲይዛቸው እና ሥራውን ለማካሄድ ወደ ባርነት እንዲወርዱ አድርጓል።
ይህ ባርነት ዓመታት እያለፈ ሲሄድ ፣ እስራኤላውያን ነጻ እንዲያወጣቸው ወደ እግዚአብሔር መጮህ ጀመሩ። እግዚአብሔርም ከባርነት ነጻ ሊያወጣቸው ሙሴን መረጠ። እግዚአብሔር ሙሴን በሚቃጠል ቁጥቋጦ ውስጥ ተገልጦለት፣ ወደ ግብፅ ተመልሶ ለሕዝቡ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ነጻ እንደሚያወጣቸው ነገረው። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሙሴም ተአምራቶቹን ለእስራኤል ለመግለጥ ፈርዖንን እንደሚጠቀም እንደተናገረው አስተውሉ።
19 ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። 20 እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። (ዘጸአት 3)
ይህንን ለአፍታ አስቡት። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለዓመታት በባርነት ተይዞ ነበር። በብዙ መከራ ውስጥ አልፈዋል። እግዚአብሔርም በዚያን ጊዜ ነጻ ሊያወጣቸው እና የራሳቸውን ሃገር ሊሰጣቸው ፈለገ። ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ግንኙነት ግን በሚፈለገው ቦታ አልነበረም። ወደ በረሃው ለመውጣት እና እግዚአብሔር ወደመረጠላቸው ምድር ለመጓዝ መንፈሳዊ ዝግጁነት አልነበራቸውም። ሊያሸንፉት የሚገቡ ጠላቶች እና የሚዋጓቸው ታላላቅ ጦርነቶች ነበሩ። የእግዚአብሔር ህዝብ ለዚህ ዝግጁ ከሆኑ፣ስለ አምላካቸው ኃይል እና ስልጣን የበለጠ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። የከነዓንን ምድር በራሳቸው ማሸነፍ አይቻሉም ስለሆነም በእነርሱ የሚሰራ የእግዚአብሔር ኃይል ያስፈልጋቸዋል። እግዚአብሔር ኃይሉን ሊያሳያቸው ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ የመረጠው በምድር ላይ በጣም ኃያል በሆነው ፈርዖን በኩል ነው። በተከታታይ ክስተቶች፣እግዚአብሔር እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ለሕዝቡም ሆነ ለግብፃውያን ያሳያቸዋል።
በዘጸአት 7:3-5 ያለውን የእግዘአብሔር ቃል አድምጡ፡
3 እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ በግብፅ ምድርም ድንቄንና ተአምራቴን አበዛለሁ። 4 ፈርዖንም አይሰማችሁም፥እጄንም በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴንም የእስራኤልን ልጆች ሕዝቤን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ አገር አወጣለሁ። 5 ግብፃውያንም፥ እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው ባወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆነሁ ያውቃሉ። (ዘጸአት 7)
በቁጥር 3 ላይ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ እንዳደነደነ አስተውሉ። በዚህ ውስጥ እግዚአብሔር ዓላማ ነበረው። ፈርዖን በግትርነት ሲቃወም ፣ የእግዚአብሔር ኃይል ለእስራኤል እና ለግብፅ ይገለጥ ነበር። ሁለቱም ሕዝቦች የእስራኤል አምላክ ተጠያቂ እንዳደረጋቸው ይመለከታሉ። እስራኤልም ለእነሱ ያለውን አስደናቂ የእግዚአብሔር ርኅራሄ ይመለከቱ ነበር።
የእግዚአብሔርን ተአምራት ለእስራኤል ለማሳየት ያገለገለው የፈርዖን ልብ ደንዳና እና ኃጢአተኛ ነበር። ሕዝቡ ይህንን በእግዚአብሔር እና በፈርዖን መካከል ያለውን ግጭት በማየት አምላካቸው የግብፅን ሕዝብ እያንበረከከ እንደሆነ አስተዋሉ። የእግዚአብሔር ኃይል የግብፅን ምድር ሲያጠፋ ተመለከቱ። ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር እጅ ፈርዖን እየደከመ ሲሄድ ተመለከቱ። በመጨረሻም ከባርነት ምድር ነጻ የሚወጡበት ቀን ሲደርስ አምላካቸው እጅግ ኃያል አምላክ መሆኑን አወቁ። በፈርዖን በኩል፣እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ ኃይሉ እና ርህራሄው አስተምሯል። የግብጹ ፈርዖን የእግዚአብሔር ተአምራቱን ለሕዝቡ የሚገልጽበት መሣሪያ ነበር።
ከመካከላችን እግዚአብሔር ተአምራቱን የሚገልጥበት መሣሪያ ለመሆን የማይመኝ ማነው? እግዚአብሔር እኛን በሚጠቀምበት ጊዜ እርሱ በመልካምነታችን ምክንያት በእኛ ለመሥራት እንደመረጠ ማሰብ የለብንም። የፈርዖን ምሳሌ ይህንን ሃሳብ ያጠናክራል። ፈርኦን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላ ሰው ነበር። እግዚአብሔርን ይቃወም ነበር ስለሆነም ከእርሱ ጋር ባለመስማማት የእግዚአብሔር ታላላቅ ምልክቶች እና ተአምራት የሚገለጡበት መሣሪያ ነበር። እግዚአብሔር ተጠቅሞባችኋል ማለት ለእግዚአብሔር ቅርብ ናችሁ ማለት አይደለም። ተዓምራቱን ለመግለጥ እርሱን የሚቃወሙትን እንኳን ሊጠቀምባቸው ይችላልና።
ናቡከደነፆር እና የእስራኤል ፍርድ
ናቡከደነፆር ሌላው እግዚአብሔር የተጠቀመበት የአህዛብ ንጉሥ ምሳሌ ነው። የእስራኤል ሕዝብ በከነዓን ምድር ሲሰፍሩና እንደ ሕዝብ ሲመሠረቱ ብዙም ሳይቆዩ አምላካቸውን ረሱ። የእግዚአብሔር ቁጣ በእነሱ ላይ ነደደ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመቅጣት እርሱን የማያውቅ ንጉሥን ለመጠቀም መረጠ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ለዚህ ዓላማ እግዚአብሔር የመረጠው መሣሪያ ሆነ። በኤርምያስ 25 ላይ የእግዚአብሔርን ንግግር አዳምጡ
8 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቃሌን አልሰማችሁምና 9 እነሆ፥ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናብከደነዖርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመደነቂያና ለማፍዋጫም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። (ኤርምያስ 25)
በተለይ በቁጥር 9 ላይ ናቡከደነፆር የእግዚአብሔር አገልጋይ ተብሎ እንደተጠራ አስተውሉ። ሕዝቡን እንዲያስተካክል በእግዚአብሔር ተመረጠ። እግዚአብሔር የሚፈርድበት ሃገር እስራኤል ብቻ አልነበረም። በኤርምያስ 27 ላይ ነቢዩ ለኤዶም፣ ለሞዓብ፣ለአሞን፣ለጢሮስና ለሲዶና ነገሥታት አንድ ቃል ሰጥቷቸዋል። ለእነዚህ ሃገራት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ቃል አድምጡ፡
5 ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። 6 አሁንም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ ይገዙለትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 7 የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን ያስገዙታል። (ኤርሚያስ 27)
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደገና የእግዚአብሔር አገልጋይ ተብሎ ተጠርቷል። እንደ ተመረጠ አገልጋይ ፣ እግዚአብሔር በገዛ ሕዝቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ባሉት ነገሥታት ላይ ለመፍረድ ይጠቀምበታል። እነዚህ ሃገራት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ናቡከደነፆርን ያገለግሉ ነበር።
ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ወደ ጦርነት ሲሄዱ፣ጌታ በብዙ ሃገራት ላይ ድልን ሰጣቸው። የእግዚአብሔር ሕዝብም በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰደ። በይሁዳ የቀሩት ናቡከደነፆርን ፈርተው ስለነበር በዮሐናን መሪነት ስር በስደት ለመኖር ወደ ግብፅ ሸሹ (ኤርሚያስ 43፡1-7 ተመልከቱ) ። ጌታ እነዚህን የይሁዳ ስደተኞች በአገልጋዩ በኤርምያስ በኩል አንድ ቃል ሰጣቸው። ኤርምያስን በግብፅ ታያኔስ በሚገኘው የፈርዖን ቤተ መንግሥት መግቢያ ላይ አንድ ትልቅ ድንጋይ እንዲያስቀምጥና ይህን ቃል እንዲናገር ነገረው:
10 እንዲህም በላቸው፦የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ልኬ ባሪያዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆር አመጣለሁ፥ ዙፋኑንም እኔ በሸሸግኋቸው በእነዚህ ድንጋዮች ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ማለፊያውን ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል። 11 መጥቶም የግብጽን ምድር ይመታል፥ ለሞትም የሚሆነውን ለሞት፥ ለምርኮም የሚሆነውን ለምርኮ፥ ለሰይፍም የሚሆነውን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል።12 በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል ያቃጥላቸውማል ይማርካቸውማል፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም በሰላም ይወጣል። 13 በግብጽም ምድር ያለውን የሄልዮቱን ከተማ ሐውልቶች ይሰብራል፥ የግብጽንም አማልክት ቤቶች በእሳት ያቃጥላል። (ኤርምያስ 43)
እንደገና እግዚአብሔር “ባሪያዬ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን” እንደሚልክ ፍርዱን በግብፅ ሕዝብ ላይ እና በእውነተኛው አምላካቸው ሳይሆን በእርሱ ባመኑት ሕዝቡ ላይ ፍርዱን ይፈጽም እንደነበር አስተውሉ።
እግዚአብሔር በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለናቡከደነፆር ኃይለኛ በሆነ መንገድ ራሱን ይገልጥ ነበር። በስልጣኑ ከፍታ በጣም ይመካ ነበር። እንደውም የራሱን ምስል አቁሞ ሕዝቡ ሁሉ ለአምልኮ እንዲሰግድ ጠየቀ። የዳንኤል ጓደኞች ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ እቶን እሳት ተጣሉ። ናቡከደነፆር በቁጣ ሲድራቅን ፣ ሚሳቅን እና አብደናጎን ከመጣሉ በፊት እቶን ከተለመደው ሰባት እጥፍ እንዲያቃጥል አዘዘ። እግዚአብሔር በዚያ እቶን እሳት ውስጥ ጠብቋቸዋል ልዩ በሆነ መንገድ መገኘቱን ገለጸላቸው። ናቡከደነፆር ወደ እቶን እሳቱ ሲመለከት ሲድራቅን ፣ ሚሳቅንና አብደናጎን እና የሚጠብቃቸውን የጌታ መልአክ መገኘቱን አየ። ይህ በናቡከደነፆር ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
እግዚአብሔር ደግሞ ለናቡከደነፆር በሕልም ራሱን ይገልጥ ነበር (ዳንኤል 4:19-27 ተመልከቱ) ። በዚያ ሕልሙ ፣ እግዚአብሔር ከሰዎች ተለይቶ እንደሚሰደድ፣ራሱን አዋርዶ ትሁት እስኪሆን ድረስ እና ኩራቱ እስኪጠፋ ድረስ መኖሪያው ከምድር አራዊት ጋር እንደሚሆን ተናገረው (ዳንኤል 4፡31-32 ተመልከቱ) ።
እግዚአብሔር በናቡከደነፆርን ተጠቀመ ባሪያውም እንደሆነ ጠራው። እግዚአብሔር መገኘቱን በኃይል እና አስደናቂ በሆኑ መንገዶች አሳይቶታል። እግዚአብሔር በሕልም ይናገረው እንዲሁም የጌታንም መልአክ ይገለጥለት ነበር። የኃጢአታቸውን ውጤት እንዲያውቁ እና እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመመለስ የተጠቀመበት ከእስራኤል ሕዝብ ያልተገኘ ንጉስ ነው።
ቂሮስ እና የእስራኤል መመለስ
ለሙሴ ዘመን ሰዎች ተአምራቱን ለመግለጥ እግዚአብሔር ፈርዖንን ተጠቅሟል። በኤርምያስ ዘመን ሕዝቡን ከሐጢአታቸው ለመመለስ የባቢሎኑን ንጉስ ናቡከደነፆርን ተጠቅሟል። እግዚአብሔርም የፋርስን ንጉሥ ደግሞ በተለየ መንገድ ተጠቅሞበታል።
ከናቡከደነፆር ዘመን በኋላ የፋርስ መንግስት ባቢሎንን ድል አድርጎ የአይሁድ ምርኮኞችን ወረሰ። ንጉሥ ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ በኢሳይያስ 45 ውስጥ ስለ ቂሮስ ተናግሯል። ስለዚህ አረማዊ ንጉሥ ምን እንደሚል ስሙ፡
1 እግዚአብሔር ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦
2 በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም ትክክል አደርጋለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤
3 በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ።
4 ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቍልምጫ ስምህ ጠራሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም።
5-6 እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።
በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለፋርስ ንጉሥ ለቂሮስ የተሰጡ አንዳንድ ኃይለኛ ተስፋዎች አሉ። በቁጥር 1 ላይ እግዚአብሔር ለቀባሁት ብሎ እንደጠራው አስተውሉ። እሱ ለተወሰነ ዓላማ ተመርጧል። እግዚአብሔር የቂሮስን ቀኝ እጅ ይዞ ነበር (ቁጥር 1) ። ይህ የእግዚአብሔርን ሞገስ እና በእርሱ ላይ ያለውን ኃይልን የሚያመለክት ነበር። በቁጥር 2 እግዚአብሔር በፊቱ እንደሚሄድ ቃል ገብቷል። ቂሮስን ባያውቀውም ቂሮስን በስሙ ጠርቶ አስታጠቀው (ቁጥር 5) ። እርሱ ፣ የእስራኤል አምላክ እና ጌታ እንደ ሆነ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ሰዎች እርሱን እንዲያውቁ ቂሮስን በኃይል አስታጠቀው (ቁጥር 5-6)። በቁጥር 5 ላይ እግዚአብሔር በኢሳይያስ በኩል የተናገራቸው ቃላት ትርጉም “እኔን ባታውቀኝም አስታጠቅሁህ፥” የሚሉ ናቸው።
ጌታ አምላኩን የማያውቅ ፣ ግን ስሙን በአህዛብ ላይ ለመግለጥ የተመረጠ አረማዊ ንጉሥ ነበር። እግዚአብሔር ይህንን ሰው በኃይል አስታጥቆ በምድር ላይ ዓላማውን ለማሳካት እና ለስሙ ክብር ለማምጣት ይጠቀምበታል።
ጌታ ልቡን ያነሳሳው በቂሮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ነበር። በመጀመሪያው ዓመት ያወጣውን አዋጅ አዳምጡ፡
23 የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም ይውጣ ብሎ በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አደረገው። (2ኛ ዜና 36)
ጌታ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲሰሩ የእስራኤልን ምርኮኞች እንዲፈታ እና ወደ ሃገራቸው ይመልሳቸው ዘንድ ቂሮስ ልብ ላይ አኖረው። ይህንን ለማሳካት ቂሮስ ከናቡከደነፆር የሰረቃቸውን ሃብቶች በሙሉ ለቀቀ። እነዚህ ሃብቶች ወደ እስራኤል ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና የመገንባቱ ሥራ በዕዝራ ብቁ በሆነ አመራር ተጀመረ።
ቂሮስ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ የእግዚአብሔር መሣሪያ ነበር። በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠራ ድጋፍ አድርጓል። ለዚህም ዓላማ በእግዚአብሔር ተጠርቷል። የእስራኤልን አምላክ በግል ሕይወቱ ባያውቀውም፣ ነገር ግን ሕዝቡን ወደ ምድራቸው ለመመለስ የእግዚአብሔር መሣሪያ ነበር።
እግዚአብሔር እሱን የማያውቀውን ቂሮስን መጥራቱ እና እንዲህ ዓይነቱን አስደናቂ ተሃድሶ እንዲያከናውን ማስታጠቀቁ እንዴት አስደናቂ ነው። ለሰባ ዓመት በግዞት ከቆዩ በኋላ፣በቂሮስ ባርኮት የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደገና ወደ ትውልድ አገራቸው ተመለሱ። እግዚአብሔር በቀኝ እጁ የማያውቀውን ሰው ወስዶ በዚህ መንገድ ልቡን የሚያነሳሳው ለምንድ ነው? በአረማዊ ንጉስ ልብ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ሸክም ለምን ያኖራል? በእግዚአብሔር ዘንድ የጸጋ ተግባር ነበር። እርሱ የመረጠውን ይጠቀማልና።
እነዚህ ጥቅሶች የሚያሳዩት እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ያለውን ታላቁን ዓላማውን ለማሳካት እሱን የሚወዱትን ብቻ የሚጠቀም ብቻ እንዳልሆነ ነው። ልቡ በእግዚአብሔር ላይ የደነደነውን ፈርዖንን ኃይሉንና ርህራሄውን ለእስራኤል ለመግለጥ ተጠቅሞበታል። ናቡከደነፆርን ተጠቅሞ በሕዝቡ ኃጢአት ላይ ለመፍረድ ተጠቅሞበታል። እርሱን የማያውቀውን ቂሮስን ሕዝቡን ወደ በረከት ለመመለስ ተጠቅሞበታል። እግዚአብሔር እኛን ሊያነጋግረን ወይም በማንኛውም መንገድ ሊሞግተን እንደሚችል ማወቅ አለብን። ለሕይወታችሁ ወዳዘጋጀው ጥልቅ መገለጥ እና ዓላማው ሊያመጣችሁ የማያምን ሰውን እንኳን ቢጠቀም ያስገርማችኋልን? እግዚአብሔር እኛ በምንረዳቸው መንገዶች ነገሮችን በመሥራት ብቻ የተወሰነ አይደለም። እግዚአብሔር አንድን ሰው መጠቀሙ ያ ሰው ወደ እርሱ መቅረቡን የሚያመለክት አይደለም። በእርግጥ እግዚአብሔር እርሱን የማያውቁ ሰዎችን ለመጠቀም ሊመርጥ ይችላልና። በእግዚአብሔር መጠቀምን እርሱን ከማወቅ እና ከእሱ ጋር ተስማምቶ ከመሄድ ጋር አታምታቱት።
ለምልከታ፡
• ፈርዖን ከእስራኤል አምላክ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ነበር? እግዚአብሔር ታዕምራቱን ለሕዝቡ ለመግለጥ እንዴት ተጠቀመበት?
• ፈርዖን እግዚአብሔር ስለተጠቀመበት ኩራት ሊሰማው ይችላልን?
• ናቡከደነፆር እና ባቢሎናውያን ጨካኝ ተዋጊዎች በመባል ይታወቁ ነበር። እግዚአብሔር እንዴት ተጠቀመባቸው?
• እግዚአብሔር ናቡከደነፆርን አገልጋዬ ብሎ ጠርቶታል። ይህ ማለት ናቡከደነፆር ከእስራኤል አምላክ ጋር በትክክለኛው ግንኙነት ውስጥ ነበር ማለት ነው?
• ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ባይኖረንም አሁንም እግዚአብሔር ሊጠቀምብን ይችላል?
• እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ በረከታቸው እና ወደ አገራቸው ለመመለስ የፋርሱን ቂሮስን እንዴት ተጠቀመበት? ቂሮስ እግዚአብሔርን ያውቅ ነበር?
• እግዚአብሔር ዓላማውን ለማሳካት በሚጠቀምበት ዓይነት ሰው ይወሰናልን?
ለጸሎት፡
• ጌታ በምድር ላይ ያለውን ዓላማውን ለመፈፀም የመረጠውን ማንኛውንም ሰው መጠቀም ስለሚችል እግዚአብሔርን አመስግኑት።
• እርሱን በማያውቁት ሰዎች እጅ እንኳን በረከቶቹ ወደ አናንተ በሚመጣበት ጊዜ ጌታን አመስግኑት።
• እርሱ ከውድቀቶቻችን እና ከስህተቶቻችን እንደሚበልጥ እና ድክመቶቻችን ቢኖሩም ሥራው ስለሚቀጥል ጌታን አመስግኑት።
• ፍሬያማ በሆኑ ግን ታማኝ ባልሆኑት ሰዎች እንዳትታለሉ ጌታን ጥበብና ማስተዋል እንዲሰጣችሁ ጸልዩ።
ምዕራፍ 8 - ኢየሱስ የመረጣቸው ሰዎች
እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ሊጠቀምባቸው የመረጣቸውን የተለያዩ የብሉይ ኪዳን ሰዎችን ተመልክተናል። በዚህ ምዕራፍ ደግሞ ኢየሱስ በዘመኑ የመረጣቸውን አንዳንድ ሰዎች መመልከት እፈልጋለሁ።
ጴጥሮስ
ጴጥሮስ ሥራው ዓሣ አጥማጅ ነበር (ማቴዎስ 4፡18 ን ተመልከቱ) ። አንድ ቀን ኢየሱስ በባሕር አጠገብ ሲጓዝ ጴጥሮስንና ወንድሙን እንድርያስን ተመለከተ። እርሱም እንዲከተሉት እና ደቀመዛሙርቱ እንዲሆኑ ጠራቸው። ጴጥሮስ የጌታ ኢየሱስ ተከታይ ከመሆኑ በፊት ስለ እርሱ ብዙ ባናውቅም፣ወንጌላት ስለዚህ ደቀመዝሙር አንዳንድ አስፈላጊ ዝርዝሮችን ያስተምሩናል።
ጴጥሮስ ወደ አዕምሮ የመጣውን ሁሉ የሚናገር ሰው ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ ኢየሱስ ለደቀመዛርቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ እና በዚያችም ከተማ ብዙ መከራ እንደሚቀበል ይነግራቸዋል፡፡ ጴጥሮስም ለዚህ ንግግሩ ኢየሱስን ሲገስጸው አንመለከታለን፡
22 ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ፦ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። (ማቴዎስ 16)
ኢየሱስ ለጴጥሮስ ተግሣጽ የሰጠው ምላሽ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ለአንድ ግለሰብ ከተነገሩት ጠንካራ መግለጫዎች ውስጥ አንዱን ነው፡
23 እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። (ማቴዎስ 16)
እነዚህ ቃላት በጴጥሮስ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መገመት እንችላለን። ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማደናቀፍ በሰይጣን ስለተጠቀመበት ይከሰዋል።
ጴጥሮስ እንዲሁ በጣም ችኩል ነበር። ወታደሮቹ ኢየሱስን ሊይዙትና ሊወስዱት ሲመጡ ፣ ዮሐንስ 18:10 ጴጥሮስ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮውን እንደቆረጠ ይነግረናል። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ጴጥሮስን ገስጾ ሰይፉን እንዲያስወግድ ነገረው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የጴጥሮስ ተፈጥሯዊ ምላሽ ከእግዚአብሔር ሃሳብ በጣም የተለየ ነበር።
ጴጥሮስ በእምነቱ ጽኑ እንደነበር አምኖ ነበር። ኢየሱስ ስለ ሞቱ ሲናገር፣የጴጥሮስ ምላሽ “ከአንተ ጋር ለመሞት ዝግጁ ነኝ” (ዮሐንስ 13:31) የሚል ነበር። ማቴዎስ 26:69-75፣ሆኖም፣ኢየሱስ ከታሰረ በኋላ፣ጴጥሮስ ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ እንደነበር ይናገራል። በዚያ ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ ጴጥሮስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑን አወቁ። ጴጥሮስም ኢየሱስን እንደማያውቀው ሦስት ጊዜ ካደ። የማቴዎስ ገለጻ ለሦስተኛው ክህደት ትርጉም ይሰጣል፡
74 በዚያን ጊዜ፦ ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።
ጴጥሮስ ጌታን ለሦስተኛ ጊዜ ሲክድ በራሱ ላይ ይራገም እና ይምል እንደነበር ማቴዎስ ሲናገር አስተውሉ። ጴጥሮስ በዚያ ምን ያደርግ ነበር? ጴጥሮስ በዚያ በነበሩት ሁሉ ፊት መሐላ እየፈጸመ ነበር። የሚዋሸው በራሱ ላይ እርግማን በመጥራት ነው። “የምናገረው ውሸት ከሆነ እኔ ርጉም ልሁን - ይህን ኢየሱስ የምትሉትን ሰው አላውቀውም።” እያለ ይምል እና ይገዘት ነበር፡፡ ይህ ከባድ ክህደት ነው።
እንግዲህ ጌታ የእርሱ ደቀመዝሙር እንዲሆን የመረጠው ሰው ይህን ደካማ ሰው ነው። የኢየሱስ ተከታይ ቢሆንም ግልጽ እና ችኩል ነበር። በእምነቱ ጽኑ እንደነበር ያስብ ነበር፤ነገር ግን ፈተና ሲገጥመው ኢየሱስን እንኳን እንደማያውቀው ለመናገር በቃ። እግዚአብሔር ግን ከጴጥሮስ ጋር ጉዳዩን አልጨረሰም ነበር። በቃል እና በተግባር ደካማ ቢሆንም፣መንፈስ ቅዱስ ጴጥሮስን በኃይል ተጠቅሞበታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ያመጡ ስብከቶችን ሰብኳል። ለጌታ ክብር በአብያተክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። የእሱ መልዕክቶች ለጌታ ክብር በዓለም ዙሪያ ባሉ ሰዎች ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።
ሳምራዊቷ ሴት
ኢየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ አንድ ቀን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት። እምነታቸውን ጠንካራ ስላልሆነ እና ድብልቅ ዘር ስለሆኑ ሳምራዊያን በአይሁዶች ይጠሉ ነበር። ኢየሱስ በአንድ ጉድጓድ አጠገብ ለማረፍ ተቀመጠ፣ከዚያም ውሃ ልትቀዳ የመጣችን አንዲት ሴት አገኘ። እንግዲህ ኢየሱስ ከእርሷ ጋር ያደረገው ውይይት የሴቲቱን ሕይወት ሁሉ ገለጠ። አምስት ባሎች ነበሯት ሆኖም አሁን አብራ የምትኖረው ሰው ባሏ አልነበረም። በኅብረተሰብ የተገለለች እና ከሥነ ምግባር የጎደለች ተደርጋ የምትቆጠር ሴት ነበረች።
መልካም ኑሮ ባይኖራትም፣ በዚያ ቀን ከኢየሱስ ጋር ከተነጋገረች በኋላ፣ ሴቲቱ እሱ መሲሕ ነኝ ብሎ የነገራት እውነት መሆኑን አረጋገጠች። የውኃ ማሰሮዋን ከጉድጓዱ ዘንድ ጥላ ለከተማው ነዋሪዎች ለመንገር ሮጣ ሄደች። እስቲ የነገረቻቸውን አዳምጡ፡
29 ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች። (ዮሐንስ 4)
በምላሹም፤የሰማሪያ ሰዎች ኢየሱስን ለማየት መጡ፡፡ የዚህ አጋጣሚ ውጤት በዮሐንስ 4:39-42 ያለውን ያስረዳናል፡
39 ሴቲቱም፦ ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት። 40 የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ። 41 ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤42 ሴቲቱንም፦ አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።
ሴቲቱ ለሰማርያ ሰዎች የተናገረችው ንግግር ውጤት ብዙዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ አደረጋቸው። ከዚያም የከተማው ነዋሪዎች ኢየሱስ ከእነርሱ ዘንድ እንዲቆይ ጠየቁት። ኢየሱስ ለሁለት ተጨማሪ ቀናት በመካከላቸው በመሆን አገለገለ። ከዚያም ከመሄዱ በፊት ሰዎቹ ወደ ሳምራዊቷ ሴት ቀርበው ያስተዋወቀቻቸው ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ መሆኑን ለራሳቸው እንዳዩ ነገሯት።
በዚህች ሳምራዊ ሴት ምስክርነት ምክንያት ታላቅ የእግዚአብሔር ስራ ተከናወነ። እርሷ ሥነ ምግባር የጎደለው ኑሮ ትኖር ነበር ፣ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በማህበረሰቧ ውስጥ መነቃቃትን ለማምጣት የተጠቀመባት መሣሪያ ነበረች። እንደዚች ሴት ከተማን ሁሉ ለመለወጥ እግዚአብሔር ደካሞችን ሊጠቀም እንደሚችል አስባችሁ ታውቃላችሁን? እግዚአብሔር፣በምህረቱ እና በጸጋው የአኗኗር ዘይቤዋ መልካም ባይሆንም፣ከተጠላው ማህበረሰብ የመጣችውን ሴት ዓላማውን ለማሳካት ተጠቀመባት።
ነብያት እና የታዕምራት ሠራተኞች
በማቴዎስ 7:21-23 ላይ ያለውን የኢየሱስን አስደንጋጭ ቃላት እንስማ፡
21 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። 22 በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። 23 የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። (ማቴዎስ 7)
እስቲ ኢየሱስ እዚህ የተናገረውን እንመልከት። በመጨረሻዎቹ ቀናት ራሳቸውን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ተመልክተው ትንቢት በመናገር ፣ አጋንንትን በማውጣት ፣ ተአምራት በማድረግ ሕይወታቸውን ያሳለፉ በርካታ ሰዎች በፊቱ እንደሚቆሙ ይነግረናል። እነዚህ ግለሰቦች በተለያዩ አገልግሎቶቻቸው፣ትንቢት በመናገር፣ አጋንንትን በማስወጣት እና የእግዚአብሔርን ኃይል በመግለጥ ስኬታማ የሆኑ ይመስላሉ።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው እና የሚያስገርመው “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ።” የሚለው የኢየሱስ ምላሽ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ፣ በጌታ ስም ቢያገለግሉም እንዲሁም ስኬታማ ቢሆኑም የጌታ እንዳልሆኑ ያውቃሉ። በእርግጥ፣ውጫዊ ስኬት መስሎ የሚታየው ከንቱ ሆኖ ተቀመጧል።
በዚህ ምንባብ ልንሄድባቸው የምንችላቸው ብዙ አቅጣጫዎች አሉ ነገር ግን በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ ልናስተውለው የሚገባን ነገር ቢኖር ኢየሱስ በተአምራት እና ምልክቶች ኃይለኞች የሚመስሉ ብዙዎች እንዳሉ ነገር ግን ከእርሱ እንዳልሆኑ እያስተማረን ነው። እውነታው ራሳቸው በእግዚአብሔር ልጅ ነጻ ያልወጡ ቢሆኑም ሰዎችን ከሰይጣን ኃይል ለማዳን እግዚአብሔር ተጠቅሞባቸው ሊሆን ይችላል። ስኬት በሚመስል ነገር መታለል የለብንም። እግዚአብሔር እርሱን የማያውቁትን ሰዎች ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ሊጠቀምባቸው ይችላልና።
አማመኞችን በድካማቸው
በፊልጵስዩስ 1 የኢየሱስ ወንጌል ስለሄደባቸው ሰዎች ሐዋሪያው ጳውሎስ የተናገረውን አድምጡ፡
15 አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤16 እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥17 እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። 18 ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። (ፊልጵስዩስ 1)
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ ሰዎች እንዳሉ ተገነንዝቦ ነበር። አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ተነስተው ይሰብኩ ነበር። ከወንድማቸው ወይም ከእህታቸው የበለጠ ተከታዮችን ለማግኘት የሚሞክሩ ነበሩ። ወንድማቸው በተሻለ ሁኔታ ከተቀበለ ወይም ብዙ አማኞች ቢያገኝ ይቀኑ ነበር። እነዚህ ምክንያቶች ለጌታ የማይገቡ እና በእውነተኛ ሰባኪ ልብ ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው ነበሩ። ሆኖም፣ጳውሎስ ለዚህ ምላሽ መስጠቱን አስተውሉ- “…በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።” (ፊልጵስዩስ 1፡18) ። አያችሁ፣ ጳውሎስ እግዚአብሔር ስለ ወንጌል አገልግሎት መልካም ዓላማ ባላቸው ሰዎች ላይ ብቻ እንዳልተመሠረተ ተረድቷል። እነዚያ ሰዎች ከምንም ሃሳብ ተነስተው ቢሰብኩም የወንጌሉ መልዕክት ወጥቶ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነበር። እነዚህ ግለሰቦች በውስጣቸው ስላለው ከንቱ ዓላማ በእግዚአብሔር ፊት መልስ ይሰጣሉ፣ነገር ግን በተሳሳተ ምክንያት በሚያገለግሉ ሰዎች ምክንያት የመልዕክቱ ኃይል አልቀነሰም።
ድካሞቻችን ቢኖሩም የእግዚአብሔር ቃል ይሰበካል። ድካም ወይም ውስንነት በቃሉ ኃይል ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር አይችልም። ከቅንአትና ከክርክር የተነሳ ክርስቶስን መስበክ የወንጌልን ኃይል በሚሰሙት ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም። የተሸከሙት ዕቃዎች ደካማ ቢሆኑም የእግዚአብሔር ቃል ንጹህና ጠንካራ ሆኖ ይቆያል።
አዲስ ኪዳን የወንጌልን ኃይለኛ መልዕክት በሚሸከሙ የሸክላ እቃዎች ምሳሌ ተሞልቷል። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ለሕይወታቸው ካዘጋጀው ክብር የጎደሉ ናቸው፣ነገር ግን እውነትን ለማወጅ በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ ያሉ መሣሪያዎች ነበሩ። አንድ ጊዜ ወንጌሉ ከታወጀ በኋላ ያ እውነት ሥር ሰዶ ሥራውን ይሰራል። ወንጌሉን ተሸክመው ወደ አሕዛብ የሚወስዱት ደካማ ሠራተኞች ቢሆኑም የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደፊት ስለሚሄድ አመስጋኞች መሆን ያስፈልገናል።
ለምልከታ፡
• ጴጥሮስ እንደ ኢየሱስ አማኝ ደካማነቱን ያሳየው እንዴት ነው? ይህ ጌታ እሱን እንዳይጠቀምበት አግዶታልን?
• የሳምራዊቷ ሴት ኑሮ ምን ነበር? እግዚአብሔር እሷን የተጠቀመው እንዴት ነው? ከደቀ መዛሙርቱ ይልቅ እግዚአብሔር ይህችን ሴት የተጠቀመው ለምን ይመስላችኋል?
• በእውነት ጌታን የሚያገለግሉ ሁሉ የእርሱ ናቸውን? የእርሱ ሳንሆን ኃይለኛውን የእግዚአብሔርን ሥራ ለመስራት ጌታ ሊጠቀምብን ይችላልን?
• የወንጌል መልዕክት በትክክለኛው አስተሳሰብ ካልተሰበከ ኃይሉን ያጣልን?
ለጸሎት፡
• ኢየሱስን ክዳችሁ ታውቃላችሁን? እናንተን ይቅር ለማለት እና በአገልግሎቱ ውስጥ ሊጠቀምባችሁ ፈቃደኛ ስለሆነ ጌታን አመስግኑ?
• ያንን መልዕክት በሚሸከሙት የሸክላ እቃዎች ደካማነት የወንጌል መልዕክት እና የመለወጥ ኃይሉ ስለማይቀንስ ጌታን አመሰግናለሁ።
• ውድቀቶቻችሁ እና ድክመቶቻችሁ ቢኖሩም እግዚአብሔር በዚህ ዓለም እና በመንግስቱ ለእርሱ ተጽዕኖ ታሳድሩ ዘንድ እንዲጠቀምባችሁ ጸልዩ።
ምዕራፍ 9 - ዓለማዊ ስኬት እና ታማኝነት
እስካሁን በዚህ ጥናት ውስጥ እግዚአብሔር ለክብሩ ሊጠቀምባቸው የመረጠውን የተለያዩ ሰዎችን ተመልክተናል። እነዚህ ግለሰቦች ፍፁም አልነበሩም። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንኳ አያውቁም ነበር፤ሌሎቹ ደግሞ በእርሱ ላይ ያመጹ ነበሩ። እግዚአብሔር የተራ ሰዎችን ጥንካሬ ሲጠቀም አይተናል፣ ነገር ግን እንዲሁ ድክመታቸውን እና አመፃቸውን ደግሞ ሲጠቀምም ተመልክተናል።ይህ እንግዲህ እግዚአብሔር ስለሚጠቀምበት ዓይነት ሰው ምን ያስተምረናል? ከእነዚህ ግለሰቦች ሕይወት ምን ትምህርት እናገኛለን? በዚህ ጥናት እስካሁን ያየነውን ለማጠቃለል እና ለመተግበር እሞክራለሁ።
በዚህ ጥናት ውስጥ ከዳሰስናቸው ምሳሌዎች እና ካገኘነው ጠንካራ ትምህርቶች አንዱ በፍሬያማነት እና በታማኝነት መካከል ያለው ልዩነት ነው። ብዙ ጊዜ እነዚህን ለይተን ማወቅ ይሳነናል። ፍሬያማነት እግዚአብሔር ለስሙ ክብር ሲል እና የመንግሥቱን ዓላማዎች ለመፈጸም አንድን ግለሰብ ከመጠቀም ጋር ይዛመዳል። በሌላ በኩል ታማኝነት፣መታዘዝ እና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግን ያመለክታል።
ለእርሱ ታማኝ ካልሆንን እግዚአብሔር እኛን ሊጠቀም እንደማይችል ብዙጊዜ ተነግሮናል። በዚህ ጥናት ያየናቸው ምሳሌዎች ይህንን የሚቃረኑ ይመስላሉ። እግዚአብሔር የሚሻውን ይጠቀማል። የማያምነውን ወይም አማኙን ሊጠቀም ይችላል። እየሰመጠ ባለው መርከብ ውስጥ አመፀኛውን ዮናስን ተጠቅሞ ወደ ተርሴስ ለሚሄዱ መርከበኞች ክብርን አሳየ። በጳውሎስ ዘመን ከቅንአት የተነሳ ክርስቶስን በሚሰብኩት ሰዎች ወንጌልን ለማራመድ ተጠቅሟል። በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ መዳን ለማምጣት ኢየሱስን በመሐላ የካደውን ጴጥሮስን ተጠቅሟል።
እግዚአብሔር እንዲጠቀምባችሁ ታማኝ መሆን የለባችሁም። ይህ አከራካሪ ሃሳብ ቢመስልም፣መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየን ይህን ነው። በእኛ ታማኝ አለመሆን እግዚአብሔር አይገደብም። 2ኛ ቆሮንቶስ 4:7 ወንጌል በሸክላ እቃዎች አሉን ይላል። እነዚያ የሸክላ እቃዎች ፍጹም አይደሉም። የክርስቶስን መልዕክት የተሸከመ እያንዳንዱ ሰው ጉድለት አለበት። ማናችንም እንከን የለሽ አይደለንም፣ ነገር ግን በዚህ ዓለም የክርስቶስ መሣሪያዎች ነን። ፍጹም ባንሆንም የእግዚአብሔር መንግሥት ወደፊት ይራመዳል። ይህ ታላቅ ተስፋ ሊሰጠን ይገባል።
በዓለማችን እና በአከባያችን አስከፊ የሆነ ግራ መጋባት እናያለን። ሃገር በሃገር ላይ በጦርነት ይነሳል። ወንጀል እና ዓመፅ በዙሪያችን ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች መሆን እንደሚገባቸው በአግባቡ አይመላለሱም። አማኞች በኃጢአት እና ታማኝነትን በማጉደል ይወድቃሉ። የእግዚአብሔር መንግሥት በእኛ በታማኝነታችን ላይ ብቻ እንደሚሰራ ብናምን ተስፋን ማጣት እንዴት ቀላል ይሆን ነበር። እግዚአብሔር የእስራኤል ጠላቶች የሆኑትን ናቡከደነፆርንና ቂሮስን ዓላማውን ለማስፈጸም መረጣቸው። እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ሉዓላዊ ነው። የምንፈራቸውን ጠላቶች እግዚአብሔር ለመልካም እና ለክብሩ ሊጠቀምባቸው ይችላል። እግዚአብሔር በዚህ ምድር ላይ ዓላማውን ለማሳካት ከእርሱ ጋር ፍጹም ተስማምተው የሚሄዱትን ብቻ በመጠቀም የተወሰነ ባለመሆኑ ማመስገን አለብን።
ፍሬያማነትን ከታማኝነት መለየት ያስፈልጋል። በአገልግሎት ፍሬያማ ስለሆናችሁ ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር በታማኝነት እና በህብረት እየተመላለሳችሁ ነው ማለት አይደለም። ፍሬያማነት እግዚአብሔር እኛን ለመጠቀም የመረጠበትን መንገድ ያመለክታል። በሌላ በኩል ታማኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የምንመላለስበትን መንገድ እና ለእርሱ እውነተኛ መሆናችንን ያመለክታል።
ይህ ትምህርት አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ያስነሳል። እኛ ለእርሱ ታማኝ ባልሆንን ጊዜ እንኳን እግዚአብሔር ሊጠቀምብን ከቻለ፣የታማኝነትን ሕይወት ለመኖር ለምን ያሳስበናል? ይህ ጥያቄ በሮሜ 6 ተጠይቆ ነበር፡
1 እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። (ሮሜ 6)
ሐዋሪያው ጳውሎስ ይህንን አጽንኦት በመስጠት “በፍጹም! በማለት ይመልሳል፡፡ ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? በዚህ ረገድ ላነሳቸው የምችላቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡
ስኬታማ ነገር ግን አሁንም በእግዚአብሔር ዘንድ ተጠያቂ
በመጀመሪያ ፣ በአገልግሎት በጣም ስኬታማ መሆን እንችላለን ነገር ግን አሁንም በኃጢአታችን ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ እንደምንሆን መረዳት አስፈላጊ ነው። ያዕቆብ አታላይ ነበር። ምንም እንኳን የእስራኤል አባት ቢሆንም ለዚያ የማታለል ተግባሩ ለእግዚአብሔር መልስ መስጠት ነበረበት። ዳዊት ታላቅ ንጉሥ ነበር ግን በዝሙት እና በነፍስ መግደል ለቅጣት ተዳርጓል። በተጨማሪም ልጁን አቤሴሎምን ችላ በማለቱ ምክንያት ባስከተለው መዘዝ መከራ ተቀብሏል። ተዕምራትን የሠሩ እና አጋንንትን ያወጡ የአዲስ ኪዳን ነቢያት ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም ለመለያየት ችለዋል።
እግዚአብሔር ሊጠቀምብን ይችላል ነገር ግን በሰማይ ስፍራ ላይኖረን ይቻላል። መዳናችን በሥራችን ላይ የተደገፈ አይደለምና። በክርስቶስ ምክንያት የመጣው ፍሬያማነታችንም ኃጢአታችንን ሊያስግድ አይችልም።በፍርድ ቀን ለእግዚአብሔር ብዙ መልስ መስጠት የሚገባቸው በርካታ መጋቢዎች እና ወንጌላውያን አሉ ብዬ እፈራለሁ። ምንም እንኳን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሕዝቡን ለመቅጣት የእግዚአብሔር መሣሪያ ቢሆንም፣እነርሱን በያዘበት መንገድ አሁንም ለእግዚአብሔር መልስ መስጠት ነበረበት።
የተሳካ አገልግሎታችን ስለ ኃጢአታችን ተጠያቂ ላለመሆናችን ዋስትና አይደለም። አሁንም በእግዚአብሔር ፊት መልስ ልንሰጥ እንቆማለንና። በአገልግሎት በጣም ፍሬያማ ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ነገር ግን በልባችሁ ኩራት እና ከአገልግሎታችሁ በስተጀርባ ባለው ስሜት እና ሃሳብ የተነሳ በሃፍረት በጌታ ፊት ለመቆም የግድ ይሆናል። ስኬታችን ጥፋታችንን ፈጽሞ አይሽረውምና።
ሽልማት የተዘጋጀው ለፍሬያማነት ሳይሆን ለታማኝነት ነው
እዚህ ላይ ልናነሳው የሚገባን ሁለተኛው ነጥብ እግዚአብሔር ፍሬያማነትን ከታማኝነት በላይ ዋጋ አይሰጠውም። በሐዋርያው ዮሐንስ በኩል የተነገረውን የኢየሱስን ቃል አዳምጡ፡
10 ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። (ራዕይ 2)
እዚህ ቃል የተገባው ሽልማት እስከ ሞት ድረስ ለታመኑት ነው።
ብዙ ሚስዮናውያን ለድካማቸው ፍሬ ሳያዩ ጌታን በታማኝነት አገልግለዋል። በርካታ ሰዎች ጌታን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው እንዲቀበሉ ምክንያት ሆነዋል፤ሌሎች ደግሞ በዚህ ምድር ላይ የመኖር እና አዳኛቸውን የማገልገል ዕድል ሳይሰጣቸው በእምነታቸው ምክንያት ተሰውተወዋል፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በፊት አንድ መጽሐፍ ስጽፍ በአንድ ምዕራፍ ላይ ላይ ሁለት ሰዓታት አሳለፍኩ ከዚያም ኮምፒውተሬ ድንገት ሲጠፋ የምጽፈውን ጽሑፍ እያገባደድኩ ነበር። ከዚያም እንዳይጠፋብኝ እየሰጋሁ የሰራሁትን ምዕራፍ መፈለግ ጀመርኩ፤ሆኖም ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ከኮምፒውተሬ ላይ ጠፍቶ ነበር። የእኔ የመጀመሪያ ምላሽ “ጌታ ሆይ ፣ ይህ እንዲሆን ለምን ፈቀድክ? እናም ምንም ሳልይዝ ወደቤቴ እየሄድኩ ነው፤ለዛሬ ማለዳ ሥራ የማሳየው ምንም ነገር የለም። ግራ ተጋብቼ እዚያ ስቀመጥ፣ጌታ በልቤ “ዋይኔ፣ታማኝ ነህን?” ብሎ ሲናገር ተሰማኝ። ይህን ለጊዜው አሰብኩና “ጌታ ሆይ ፣ ቃልህን እንድጽፍና እንድገልጥ ጠይቀኸኛል። ምንም የማሳየው ባይኖረኝም ዛሬ ጠዋት ያደረግሁት ይህንን ነው። በዚህ ላይ ትንሽ ሳሰላስል ማበረታቻ እና ደስታ በልቤ ውስጥ መፍሰስ ጀመረ። ታማኝ ነበርኩ። እግዚአብሔር የጠየቀኝን አደርግ ነበር። እኔ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆኔን ስለማውቅ የማለዳ ሥራ አድርጌ ምንም የማሳየው ነገር ሳይኖር ነገር ግን ከልብ በሆነ ደስታ ወደ ቤቴ ተመለስኩ።
እኔ ለማንሳት የሞከርኩት ነጥብ ምንድ ነው? በዚህ ምድር ላይ ለምታደርጉት ጥረት ሁሉ ለእግዚአብሔር የምታሳዩበት ነገር ላይኖራችሁ ይችላል እያልኩ ነው፣ ሆኖም እግዚአብሔር ታማኝነታችሁን ይመለከታል። በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ስለተናቀውንና ስለተበደለውን ነቢዩ ኤርምያስ አስባለሁ። ፍሬያማ በማይመስል አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ይታገል ነበር። እርሱን የሚሰማ ሰው ያለ አይመስልም። ያሳድዱት እና በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይቃወሙት ነበር። ለጥረቱ የሚያሳው በጣም ጥቂት ፍሬ በሆነ ጊዜ እንኳን ይህ ሰው ለእግዚአብሔር ጥሪ ባለው ታማኝነት የተነሳ የሚያገኘውን አስደናቂ ሽልማት አስባለሁ። ፍሬን በማናይ ጊዜ ታማኝ ሆኖ መቆየት ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶች ፍሬ ፍለጋ ታማኝነታቸውን ይተዋሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ቦታን እንድንይዝ ወይም በጣም ትንሽ እንቅስቃሴን በምናይበት ስፍራ እንድንቆይ ይጠራናል። ታማኝነታችን ትንሽ ፍሬን ወደምናይበት በረሃማ ስፍራ ሊመራን ይችላል። ፍሬን ያለማቋረጥ የሚሹ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የታማኝነት ፍላጎታቸው ይታወራል። ፍሬያማ ለመሆን ያላችሁ ፍላጎት በታማኝነት መኖርን እንዲከለክላችሁ አትፍቀዱ።
በዚያ የመጨረሻ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ስትቆሙ፣እርሱ የእናንተን አገልግሎት ከጓደኞቻችሁ አገልግሎት ጋር አያወዳድርም። እሱ ስንት ሰዎችን በወንጌል እንደደረሳችሁ አይቆጥርም። እርሱ የሚያስበው ታማኝ እና ታዛዥ ስለመሆናችሁ ብቻ ይሆናል። ሽልማታችሁ የሚመጣው ለእሱ ካላችሁ ታማኝነት ጋር እንጂ አገልግሎታችሁ በዓለም ፊት ምን ያህል የተሳካ መስሎ በመታየቱ አይደለምና።
ፍሬያም ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት የሌለው ሕይወት
ይህንን ምዕራፍ ከማብቃቴ በፊት ላነሳው የምፈልገው አንድ የመጨረሻ ነገር አለ። ፍሬያማነት ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ሕብረት ዋስትና አይሆንም። ቀደም ሲል እንዳየነው፣እግዚአብሔር ታዕምራቱን ለእስራኤል ለመግለጥ ይዋጋው በነበረው ፈርዖን ተጠቅሟል። የክርስትና ሕይወት የሚለካው ለእግዚአብሔር ባደረግነው ጥረት መጠን ወይም አገልግሎታችን በምን ያህል ሁኔታ ስኬታማ እንደሆነ ሳይሆን ከእርሱ ጋር ባደረግነው የሕብረት ጉዞ እና ቅርበት ብቻ ነው።
የጋብቻ ጥራት የሚለካው ያ ጋብቻ በፈጠራቸው ልጆች ብዛት ሳይሆን በባልና ሚስት መካከል ባለው ግንኙነት ነው። ሆኖም በክርስትና ሕይወት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ያለንን ሕብረት እስከናጣ ድረስ በስኬት እና በአገልግሎት ላይ እናተኩራለን። ትኩረቱን ከክርስቶስ ህልውና እና የግል ህብረት ላይ ያነሳ የክርስትና ሕይወት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ሁሉ የተሳሳተ ይሆናል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስኬታማ የሆነ አገልግሎት ነበረው፣ነገር ግን ለሕይወቱ ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ በማስመልከት ለፊልጵስዩስ የነገረውን አዳምጡ፡
7 ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። 8-9 አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤(ፊልጵስዩስ 3)
ሐዋርያው ለእሱ አስፈላጊ የሆነውን ሲመለከት እና ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሲነጻጸር ሁሉንም ነገር እንደ ከንቱ ነገር መቁጠሩን ለፊልጵስዩስ ሰዎች ይነግራቸዋል። ይህ የጳውሎስ ሕይወት ዋና ትኩረት ነበር። ክርስቶስን ይበልጥ ማወቅ ይፈልግ ነበር። የተቀረው ሁሉ ለእርሱ ሁለተኛ ነገር ነው። ብዙጊዜ የክርስትናን ሕይወት የምንመዝነው ስለ አገልግሎት እና ፍሬያማነት እንጂ መጀመሪያ ክርስቶስን ማወቅ እና ከእሱ ጋር ስላለ ሕብረት አይደለም። ፍሬያማ አገልግሎት የሚመጣው ክርስቶስን ከማወቅ ነው።
ፍሬያማ በመሆናችሁ ብቻ ደስተኞች ናችሁን? በሕይወታችሁ ውስጥ ያለው ግባችሁ ያ ነውን? በቁጥሮች እና ስታትስቲክ ብቻ እርካታ ይሰማችኋልን? በጣም ትንሽ ፍሬ ወደምታዩበት በረሃ ብትጠሩ ምን ትሆናላችሁ? በበሽታ ተይዛችሁ አልጋ ላይ በተኛችሁበት ጊዜ ወይም ሌላ ፍሬ ማፍራት በማትችሉበት ሁኔታ ውስጥ ስትሆኑ ከክርስቶስ ጋር ያላችሁ ሕብረት ያበቃልን? ክርስቶስ እና ከእሱ ጋር ያላችሁ ሕብረት በቂ የሚሆነው በፍሬያማ አገልግሎት ውስጥ ስትሆኑ ብቻ ነውን?
አንዳንዶች በፍሬያማ በሆኑ ምስኮች ውስጥ ያልፋሉ። ሌሎችን ደግሞ በምድረ በዳ በረሃ ውስጥ ይመራቸዋል። በሕይወት ጉዞ ውስጥ ሁለቱንም ፍሬያማ የሆነ መስክ እና ምድረ በዳ ያጋጥመናል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ አንድ የማይለወጠው እውነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እና ሕብረት ነው። ለእኛ ያለው ፍቅሩ እና መሰጠቱ ጸንቶ ይኖራል። ከእሱ ጋር ያለን ግንኙነት አስተማማኝ ነው። በዚህ መደሰት እንችላለን።
ፍሬያማ ልንሆን ዳሩ ግን ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ሕብረት ላይኖረን ይችላል። በእርግጥ ከክርስቶስ ጋር ያለን ሕብረት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ይህ ከክርስቶስ ጋር ያለው ኅብረት ለአገልግሎታችን ሁሉ መሠረት ነውና። ሕብረት ስናደርግ እርሱ በአገልግሎት ይመራናል እንዲሁም በኃይል ያስታጥቀናል። አገልግሎት እና የአገልግሎታችን ፍሬ በሕይወታችን ውስጥ የእርሱን ቦታ ፈጽሞ መውሰድ የለበትም።
ለምልከታ፡
• ለእርሱ ታማኝ ባንሆን እግዚአብሔር ሊጠቀምብን ይችላልን? አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጡ።
• እግዚአብሔር ባለመታመናችን ምክንያት ያልተገደበ የመሆኑ እውነት በዚህ ዓለም ላይ ተስፋን እንዴት ይሰጠናል? የእግዚአብሔር ዓላማ 100% ለእግዚአብሔር ታማኝ በሆኑት ላይ የተመሰረተ ቢሆን ምን ይሆናል?
• በአገልግሎት የሚኖረን ስኬታማነት ጥፋተኝነታችንን ያስወግዳልን? ስኬታማ መሆን እና አሁንም ለኃጢአተኛ ባህሪያችን እና ዓላማዎቻችን ለእግዚአብሔር መልስ መስጠት እንችላለን?
• ለስኬት የሚሰጡ ሽልማቶች ለታማኝነት ከሚሰጠው የሚለየው በምንድ ነው? እግዚአብሔር የሚሸልመን እንዴት ነው?
• ስኬታማ መሆን ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለን ያረጋግጣልን?
• ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ምንድ ነው?
ለጸሎት፡
• እርሱ ከውድቀቶቻችን እና ጉድለቶቻችን የሚበልጥ ስለሆነ እና ደካሞች ብንሆንም እንኳን ዓላማውን በእኛ ስለሚፈጽም ጌታን አመሰግኑ።
• ንስሃ ልትገቡባቸው የሚገቡ ኃጢአቶች ካሉ እግዚአብሔር እንዲያሳያችሁ ጸልዩ። ስኬት ከታማኝነት ይልቅ ለእናንተ በጣም አስፈላጊ ከሆነ እውነቱ እንዲበራላችሁ ጠይቁ።
• ሐዋርያው ጳውሎስ ቅድሚያ የሚሰጠው ክርስቶስን ማወቅ ነው፤ይህም እውነት በእናንተ እንዲሰራ ጠይቁ። አገልግሎት እና የአገልግሎት ስኬት ጣዎት ለሆኑባችሁ ጊዜያት እግዚአብሔር ይቅር እንዲላችሁ ጸልዩ።
ምዕራፍ 10 - ምስጋናውን መውሰድ
እንደ ሰው ለስኬታችን እና ፍሬያማነታችን ምስጋናውን ለመውሰድ ተፈጥሯዊ ፍላጎት በውስጣችን አለን። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ነገር ግን ሁሉም በኩራት ከተሞላ ልብ የሚመነጭ ይመስላል። ያለ እግዚአብሔር ምንም ማድረግ እንደማልችል እገነዘባለሁ፣ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊጠቀምብኝ የፈለገው አንድ ብቃት እኔ ጋር በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ እንዲሰማኝ እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር የሚጠቀምብኝ በእኔ ውስጥ ባየው መልካም ነገር እንደሆነ አስባለሁ።
“ጠንክረን ብንሞክር የበለጠ ፍሬያማ እንሆናለን፤ራሳችንን ባስተካከልን መጠን ለእግዚአብሔር የበለጠ እንጠቀመዋለን፤ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ በቀረብን ቁጥር እኛን ሊጠቀምበት ይችላል” የሚል ስሜት በእያንዳንዳችን ውስጥ አለ። ይህ ችግር ትኩረታችንን የፍሬያማነት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ላይ ያነሳል። እግዚአብሔር እኛን የሚጠቀምበት ትክክለኛ ምክንያት በማንነታችን እና በሠራነው መልካም ነገር እንደሆነ እናስባለን። ስለሆነም ምስጋናውን ለራሳችን መውሰድ እንዳለብን ይሰማናል።
በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ጉዞ እና ፍሬያማነታችን መካከል ግንኙነት እንዳለ አይካድም። በነቢዩ በሆሴዕ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አዳምጡ፡
1 እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
2 እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፤ ደምም ወደ ደም ደርሶአል።
3 ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። (ሆሴዕ 4)
በእነዚህ ጥቅሶች በእግዚአብሔር ሕዝብ ታማኝነት እና በምድሪቱ ፍሬያማነት መካከል ያለውን ግንኙነት አስተውሉ። ታማኝነት ወይም ጽኑ ፍቅር ስለሌለ ምድሪቱ ፍሬዋን አትሰጥም ነበር፣ እንስሳት፣ወፎች እና ዓሦች እየጠፉ ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝብ ታማኝ ባለመሆኑ ምክንያት በምድሪቱ ላይ እርግማን ሊመጣ ችሏል። እግዚአብሔር ግን በመታዘዝ የሚመላለሱትን ይባርካል።
በታዛዥነት የሚመላለሱትን እግዚአብሔር እንደሚባርካቸው እውነት ቢሆንም ፣ ያን ለማድረግ አይገደድም። ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ በረከት ሁሉ በእሱ የሚሆን የርህራሄ እና የጸጋ ወጤት ነውና። ከእኛ መካከል ማንም እግዚአብሔር የሚፈልገውን ፍጹም የሆነ ኑሮ መኖር አይችልም። የእኔን መታዘዝ እና ታማኝነት ለእግዚአብሔር በረከት ምክንያት አድርጌ ለመውሰድ የፈለኩትን ያህል፣ እኔ ወደ እግዚአብሔር ስቀርብ፣ አሁንም እንደጎደልኩ መገንዘብ አለብኝ። ኃጢአተኛው ልቤ ምን ማድረግ እንደሚችል አውቃለሁ። በአዕምሮዬ ዘንድ በሚገኙ በተደበቁ ክፍተቶች ውስጥ የሚሸሸጉትን ሀሳቦች አውቃለሁ። አሁንም መታረም የሚገባቸው እና ከእግዚአብሔር ዓላማ ጋር የማይስማሙ አመለካከቶች እንዳሉኝ አውቃለሁ። የኢየሱስ ይቅርታ ባይሆን ኖሮ ያለ ሃፍረት እና በደል በአብ ፊት መቆም አልችልም ነበር። ወደ ሕይወቴ የመጣው ይህ ፍሬያማ በረከት ይገባኛል ማለት እችላለሁን? በእውነት የእግዚአብሔር እዳ አለብኝ ማለት እችላለሁ?
በእውነቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር በረከቶች በእርግጥ እንደሚገባቸው የተናገሩበት አንድም ጊዜ አልነበረም። ሁልጊዜ ከእርሱ ክብር የጎደሉ ነበሩ። ይህ የእኔም ጉዳይ ነው። ለማስተካክለው ለእያንዳንዱ አመለካከት፣ በኃጢአተኛ ተፈጥሮዬ ውስጥ ማስተካከል የሚገባኝ በርካታ አመለካከቶች አሉ። በእውነቱ፣ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ በቀረብኩ መጠን ከእሱ ምን ያህል እንደራቅሁ የበለጠ እገነዘባለሁ። ከእግዚአብሔር የሚመጣ በረከት ሁሉ የጸጋው እና የርህራሄው ተግባር ውጤት ነው። እኔ የማፈራው ፍሬ ሁሉ ከእርሱ የሆነ ነው። በአገልግሎቴ ላገኘሁት ስኬት ሁሉ ለእርሱ ክብር ይገባዋል። እኔ የማይገባኝ መሣሪያ ነኝ፤እርሱ ግን በአገልግሎት እና በህይወት ውስጥ የበረከቶች ሁሉ ምንጭ ነው።
በዮሐንስ 15 ፣ ኢየሱስ ስለ አንድ የወይን ተክል እና ስለ ቅርንጫፎቹ ታሪክ ይነግረናል። በዚህ ምሳሌ ውስጥ ኢየሱስ ራሱን ከወይን ተክል ጋር አመሳስሎታል። እኛ ደግሞ ቅርንጫፎች ነን፡
5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። (ዮሐንስ 15)
ኢየሱስ በእርሱ የሚኖሩት ፍሬ እንደሚያፈሩ ያስተምረናል። ያለ እርሱ ምንም ፍሬ አንችልም። ቅርንጫፉ ከወይኑ ግንድ ሲለያይ ምን ይሆናል? ደርቆ ይሞታል። በራሱ ሕይወት የለውምና። ፍሬያማነት ሁሉ የሚመጣው ከወይኑ ግንድ ነው። ቅርንጫፉ በወይኑ ግንድ ላይ ያለውን ፍጹም ጥገኝነት እያወቀ በሚያፈራው ፍሬ ሊኩራ ይችላልን? ምክንያቱም እሱ መሣሪያ እንጂ የፍሬው ምንጭ አይደለምና። ሁሉም ቅርንጫፎች ተመሳሳይ መጠን ያለው ፍሬ አለማፍራታቸው እውነት ነው። አንዳንድ ቅርንጫፎች ከሌሎቹ የበለጠ ፍሬያማ ናቸው። ዳሩ ግን እያንዳንዱ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ላይ ጥገኛ ነው፤ያለ እሱም ፍሬ ሊኖር አይችልም። የወይኑ ግንድ የበረከት እና የፍሬያማነት ሁሉ ምንጭ ነው።
በኢሳይያስ ዘመን እግዘአብሔር ሕዝቡን እንዲህ ይላል፡
10 እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ።11 ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና፤ ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም። (ኢሳይያስ 48)
በኢሳያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል በጣም ግልፅ ነው። ክብሩን ለሌላ አይሰጥም። ለሚሠራው ሁሉ ክብርና ምስጋና የሚገባው እርሱ ብቻ ነው። እኔ በራሴ ላደርገው የማልችለውን ነገር ከእሱ ምስጋናውን መውሰድ ይገባኛልን?
ሐዋርያት ሥራ 12 የሄሮድስን ሞት ታሪክ ይተርካል። ሄሮድስ በጢሮስና በሲዶና ሕዝብ ፊት ቆሞ ድንቅ ንግግር ያደርግ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ የሄሮድስ ቃላት በጣም ኃይለኛ ስለነበር የሰሙት ሰዎች ሁሉ “የእግዚአብሔር ድምፅ እንጂ የሰው ድምፅ አይደለም” ብለው ጮኹ። (የሐዋርያት ሥራ 12:22) ሄሮድስ እነዚህን ቃላት ስለወደዳቸው ከልቡ ተቀበላቸው። የሐዋርያት ሥራ 12፡23 በእነዚያ ቃላት ክብር በመደሰቱ እና ለእግዚአብሔር እውቅና መስጠት ባለመቻሉ ምን እንደደረሰበት ያስተምረናል፡
23 ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ። (የሐዋርያት ሥራ 12)
እንዲሁም ስለ ታላቁ ንጉሥ ናቡከደነፆር በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ እናነባለን፡፡ በአንድ ወቅት በባቢሎን ቤተመንግስቱ ሰገነት ላይ ሲራመድ የመንግሥቱን ታላቅነት ተመለከተ። በበረከቶቹ ስፋት እና በጥረቱ ፍሬ አሸንፎ እንደሆነ እንዲህ አለ፡
30 ንጉሡም፦ ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ። (ዳንኤል 4)
በትምህክት የተሞላው የናቡከነጾር ቃላት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደረሰ፡፡ ውጤቱም እጅግ አሰቃቂ ነበር፡
31 ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና፦ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፦ መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤32 ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው። 33 በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። (ዳንኤል 4)
የናቡከደነፆር መንግስት ከእርሱ ተወሰደበት፡፡ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፤መኖሪያውም ከምድር አራዊት ጋር ሆነ፡፡ “ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ” (ቁጥር 32) ይህ የእርሱ ቅጣት ሆኖ ይቆያል፡፡ ናቡከደነፆር ምስጋናውን ከእግዚአብሔር በመውሰዱ እና ከእርሱ ጋር ራሱን በማስተካከሉ ምክንያት ለቅጣት ተደዳርጓል፡፡መንግስቱን የሰጠው እግዚአብሔር ነበርና፡፡ ናቡከደነፆር መጠቀሚያ መሣሪያ እንጂ ክብር ሁሉ የተገባው እግዚአብሔር ነው፡፡ ክብርን ከእግዚአብሔር ለራስ መውሰድ በጣም ከባድ ጉዳይ ነው፡፡
በኢሳይያስ 10 ለሕዝቡ የተናገረውን እግዚአብሔር ቃል አድምጡ፡
13 እርሱ እንዲህ ብሎአልና፦ አስተዋይ ነኝና በእጄ ኃይልና በጥበቤ አደረግሁት፤ የአሕዛብን ድንበሮች አራቅሁ፥ ሀብታቸውንም ዘረፍሁ፥ እንደ ጀግናም ሆኜ በምድር የተቀመጡትን አዋረድሁ፤14 እጄም የአሕዛብን ኃይል እንደ ወፍ ቤት አገኘች፤ የተተወም እንቍላል እንደሚሰበሰብ እንዲሁ እኔ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ ክንፉን የሚያራግብ አፉንም የሚከፍት የሚጮኽም የለም።15 በውኑ መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይመካልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ላይ ይጓደዳልን? ይህስ፥ በትር የሚያነሣውን እንደ መነቅነቅ ዘንግም እንጨት ያይደለውን እንደ ማንሣት ያህል ነው።
ድልን ያገኙት ከእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ በኢሳያስ 10 ሕዝቡን ያስታውሳል። ሕዝቡ የሆኑት ከእርሱ ጥበብ የተነሳ ነበር። በጦርነት ውስጥ ያገኙት ድል እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር በመገኘቱ ምክንያት የመጣ ነው። እርሱን ሊቃወም የሚችል ማንም የለምና። የእስራኤል ሠራዊት የእግዚአብሔር መሣሪያ ቢሆንም የሚኩራራበት ምክንያት አልነበረውም። መጥረቢያ አንድን ትልቅ ዛፍ ቢቆርጥ ሊኮራ ይችላልን? መጥረቢያው ያለ ሰው ዋጋ የለውምና። ምስጋና ሁሉ የሚገባው መጥረቢያውን ለሚጠቀምበት ሰው ነው።
በጌታ እጆች የምንገኝ መሳሪያ መሆን አስደናቂ እድል ነው። እድል ቢሆንም ምስጋናውን ለራሳችን መውሰድ አንችልም። ያ የእግዚአብሔር እጅ ባይረዳን ኖሮ ዋጋ ቢስ እንሆናለን። ያለ እርሱ ምንም ማድረግ አንችልምና። ለመልካም ነገሮች ሁሉ እርሱ ክብር ይገባዋል። ለመንግሥቱ የሠራሁት ማንኛውም ዋጋ ያለው ነገር ሁሉ በጸጋው ምክንያት የሆነ ነው።
ፍሬያማነታችን በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት መሆኑን መገንዘብ ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ ነው። በእኛና በእኛ በኩል ላከናወነው ሁሉ ክብር የሚገባው እርሱ ነው። እኛ ፍጹማን አይደለንም። በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ ያለን ደካማ መሣሪያዎች ነን። ጌታ ሊጠቀምብን የሚችለው በእሱ ችሎታ እና ጥበብ ብቻ ነው። ብዙ ጊዜ እንደ ናቡከደነፆር “ያደረግሁትን ተመልከቱ” ስንል ራሳችንን እናገኛለን። ከዚህ አመለካከት ንስሐ መግባት አለብን። እግዚአብሔር ክብሩን ለማንም አይሰጥምና። እኛ መሣሪያዎቹ ነን ዳሩ ግን ያንን መሣሪያ የሚቆጣጠረው እሱ ነው። ከወይኑ እንደተለየው ቅርንጫፍ፣ያለ እሱ ጠውልገን እንሞታለን። ክብርና ምስጋና ሁሉ ለእርሱ ብቻ ነውና።
ለምልከታ፡
• ለስኬቶቻችን እና ፍሬያማነታችን ምስጋናውን ለራሳችን ለመውሰድ ለምን እንፈልጋለን? ከዚህ ፍላጎት በስተጀርባ ያለው ምንድን ነው?
• በእውነት በሕይወታችን ለምናፈራው ፍሬ ክብር ይገባናል ልንል እንችላለን?
• እግዚአብሔር በሕይወታችን ላደረገው ነገር ክብርን ለራሳችን መውሰድ ምን ያህል ከባድ ነው?
ለጸሎት፡
• በሕይወታችሁ እና አገልግሎታችሁ ፍሬያማነት ክብርን ሁሉ መስጠት ትችሉ ዘንድ ጌታን ጸጋ እንዲሰጣችሁ ጸልዩ።
• ጉድለቶቻችን ቢኖሩንም እርሱ ሊጠቀምብን ስለሚችል ጌታን አመስግኑት። ለክብሩ መሣሪያ አድርጎ ስለተጠቀመባችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑት።
• ለሠራው ሥራ ምስጋና እና ክብር መስጠት ያልቻላችሁበትን ጊዜያት ጌታ ይቅር እንዲላችሁ ንስሃ ግቡ። እሱ በሕይወታችሁ ባደረገው ለራሳችሁ ምስጋናን ለመውሰድ ያላችሁን ማንኛውንም ፍላጎት እንዲያስወግድ ጠይቁ።
ምዕራፍ 11 - ዓለማዊ ስኬት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው መንፈሳዊ ጉዳዮች
በአገልግሎት ውስጥ ላሉ ወገኖች ፈተና የሚሆነው ለስኬት (በዓለም እንደሚገልጸው) ቅድሚያ መስጠት ነው። ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት እንዲኖሩን እንፈልጋለን። በሰዎች ዘንድ የሚታይ አስደናቂ እድገት እና ስታቲስቲክስ እንዲኖረን እንወዳለን። ልንረዳው ከሚገቡን ነገሮች አንዱ እግዚአብሔር ዓለማዊ ስኬትን በአገልግሎታችን ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑ ነው።
በፍሬያማነት እና በታማኝነት መካከል ያለውን ልዩነት ተመልክተናል። እግዚአብሔር በዓለም እይታ ውስጥ ምን ያህል ስኬታማ መስለን ታይተናል ከሚለው ይልቅ ለዓላማው ምን ያህል ታማኝ መሆን እንዳለብን ይናገራል። እንደ አማኝ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው።
በዚህ ጥናት እግዚአብሔር አስቸጋሪ ባህሪ ያላቸውን ሰዎች እንዴት እንደተጠቀመ ተመልክተናል። ፍሬያማ ቢሆኑም፣ዳሩ ግን እነርሱ ቅድሚ የሚሰጧቸው ጉዳዮች የእግዚአብሔር አልነበሩም። ያጠናናቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች እንደገና ለማጤን ትንሽ ጊዜ እንውሰድ።
ያዕቆብ
ያዕቆብ አታላይ ነበር። የወንድሙን የልጅነት መብት ለማግኘት ሲል ደካማ ጎኑን ተጠቅሟል። ከጊዜ በኋላ ራሱን በመደበቅ እና አባቱን በመዋሸት የወንድሙን በረከት ሰረቀ። እንዲሁም አማቱን በማታለል በበግ ሃብት ሊበለጽግ ችሏል። በእነዚህ ሁሉ ማታለያዎች ምክንያት ያዕቆብ እጅግ ባለጸጋ ሆነ፣ይሁን እንጂ ያዕቆብ በሕይወቱ እግዚአብሔር ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት ይሰጥ ነበርን? ይህ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
ሐቀኝነት እና የባህሪ ታማኝነት ከዓለማዊ ቁሳቁስ ይልቅ ቅድሚያ አይሰጥምን? በማርቆስ 8 ላይ ጌታ ኢየሱስ ለሚከተሉት የተናገረውን አዳምጡ፡
36 ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? (ማርቆስ 8)
እንዲሁም ኢየሱስ በማርቆስ 6 እንዲህ ይላል፡
24 ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። (ማቴዎስ 6)
ሁላችንም የምንወስነው ውሳኔ አለን። በህይወት ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ምንድ ነው? እንደ ያዕቆብ ዓለማዊ በረከትን እና ሃብትን በማንኛውም መንገድ ስለማግኘት እናስባለን? በዓለም ፊት ስኬታማ ለመሆን ራሳችንን በማታለል እና በማመቻመች ለመኖር እንፈቅዳለን?
ሳምሶም
ሳምሶን ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ለእግዚአብሔር እና ለዓላማው የተለየ ነበር። ይህም እንደ ናዝራዊ በአንድ የተወሰነ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ መኖርን ያካትታል። የወይን ጠጅ ወይም ብርቱ መጠጥ መጠጣት፤የሞተ ነገር መንካት እንዲሁም ጸጉሩን መላጨት አይኖርበትም።ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እነዚህን ግዴታዎች ያፌዘባቸው ይመስላል። ለእግዚአብሔር የገባውን ቃል ችላ ብሎ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ ያደርግ ነበር።
ሳምሶን ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመራ ነበር። ከዝሙት አዳሪዎች ጋር የሚታይ እና ከባዕዳን ሴቶች ጋር የሚኖር ሰው ነበር። በበቀል የተሞላ እና ፍላጎቱ እሱን ባስቀየሙት ሰዎች ላይ በበቀል መነሳት ነበር።
ሐዋሪያው ጳውሎስ በኤፌሶን 4 ላይ እግዚአብሔር ስለእኛ ያለው መሻት ምን እንደሆነ ያሳየናል፡
32 እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። (ኤፌሶን 4)
የዕብራውያን ጸሐፊ የሚከተለው ያስታውሰናል፡
30 በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። (ዕብራውያን 10)
ሳምሶን እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ በቀልን ይፈልግ ስለነበር ያሳወሩትን ይቅር ማለት አልቻለም ነበር።
ሳምሶን ምንም እንኳን እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ሰው ቢሆንም፣በሕይወቱ ውስጥ እግዚአብሔር ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ትኩረት አይሰጥም ነበር። በንዴት ውስጥ የሚኖር የበቀል ሰው ሆነ። እርሱ የሚያገለግለውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለሌሎች የሚያሳይ ሰው አልነበረም።
በአገልግሎታችን ውስጥ ሥጋዊ ቁጣ የተነሳሽነታችን ምክንያት እንዲሆን እንፈቅዳለን? የቆሰለ ኩራታችን እንዲነዳን እንፈቅዳለን? የመንፈስ ፍሬዎችን በማግፋፋት በኃጢአተኛ አስተሳሰባችን እንነሳለን? አምላካችን እግዚአብሔርን በሕይወታችን ልናከብረው ይገባዋል። በእርግጥ ቅድሚያ የምንሰጠው በሥራችን ብቻ ሳይሆን በልባችን እና በአዕምሮአችን እሱን ማክበር መሆን አለበት።
ዮናስ
የነነዌ ሰዎች በዮናስ ስብከት ምክንያት ንስሐ ሲገቡ እግዚአብሔር ይቅር አላቸው። ዮናስ ለከተማዋ ነዋሪዎች ካለው ጥላቻ የተነሳ እግዚአብሔር ይቅርታ ሲያደርግላቸው እጅግ ተበሳጨ። ወደ ነነዌ እንዲሄድ የእግዚአብሔር ጥሪ ከደረሰው ቀን ጀምሮ፣እስከ ዮናስ መጽሐፍ መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔርን እና ዓላማውን የተቃወመ ነቢይ ተደርጎ ይገለጻል። በትምክት እና በጭፍን ጥላቻ የተሞላ ነበርና።
ዮናስ በአገልግሎቱ አስደናቂ ፍሬ በሚያይ ጊዜ የእግዚአብሔርን ልብ ለሌሎች አላካፈለም። ይልቁንም የነነዌ ሰዎች አብዝቶ ይጠላ ነበር።በእነርሱ ላይ የሚሆነውን ፍርድ እና ጥፋት ይናፍቅ ነበር። በውጭ ሲታይ የዮናስ አገልግሎት ስኬታማ ይመስል ነበር፣ዳሩ ግን ልቡ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል አልነበረም። ለእግዚአብሔር ሃሳብ ራሱን ማስገዛት አልቻለም።
እግዚአብሔርን እና ለሕይወታችን ያለውን ዓላማ በመቃወም በአገልግሎት ለዓመታት መቆየት እንችላለን። ለጌታ ራሳችንን ሳናስገዛ እና ከኃጢአት ልምምዶች ሳንወጣ ማገልገል እንችላለን። በአገልግሎታችሁ ምክንያት በምትኖሩበት አከባቢ ላይ ተጽዕኖ ልታመጡ ብትችሉም ነገር ግን ልባችሁ ከእግዚአብሔር ሃሳብ የራቀ ነው። በውስጣችሁ ለስሙ የማይመጥኑ አመለካከቶች እና ውስጣዊ ፍላጎቶች አሉ። እነዚህን አመለካከቶች እናስወግድ ዘንድ የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው። እግዚአብሔር ለሕይወታችሁ ላለው ዓላማ እና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ራሳችሁን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁን? ከእርሱ ያልሆነውን ሁሉ ከሕይወታችሁ እንዲያስወግድ ትፈቅዱታላችሁን?
ዳዊት
እንደ ንጉሥ ዳዊት የተከበረና ሞገስ ያለው ንጉሥ አልነበረም። የእርሱ አመራር አገሪቱን ወደ አስደናቂ ብልጽግና መርቷታል። ይሁን እንጂ ዳዊት ኃይለኛ እና ስኬታማ ቢሆንም በሕይወቱ ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ቅድሚያ አይሰጥም ነበር። በቤተሰቡ ሕይወት ውስጥ የሆነው ሁሉ በቂ ማስረጃ ሊሆነን ይችላል።
ዳዊት በ 2ኛ ሳሙኤል 6፡22 ላይ ሚስቱን ሚልኮልን ወደ ጎን ሲገፋ እናያለን። በ2ኛ ሳሙኤል 14፡23-24 ደግሞ ልጁ አቤሴሎምን እንዳልተቀበለው እንመለከታለን። እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት ዝሙትን ሲፈጽም ተመልክተናል። ዳዊት ስኬታማ ንጉሥ ቢሆንም ሁልጊዜ በእግዚአብሔር መንገድ መጓዝ አልቻለም። በዚህ ንጉሥ ልብ ውስጥ ገና የሚከናወን ታላቅ የእግዚአብሔር ሥራ ነበር። በእርግጥ ንጉሥ ዳዊትን ወደ ራሱ ለማቅረብ ሲፈልግ እነዚህ ጉዳዮች ለእግዚአብሔር ትልቅ ጠቀሜታ ነበራቸው።
ወንጌላዊው ፊሊጶስ
ወንጌላዊው ፊልጶስ በሰማርያ ያገለግል ነበር። በዚያም ሲያገለግል የእግዚአብሔርን ኃያል ሥራ ይመለከት ነበር። ሰማሪውያን ወደ ጌታ ሲመጡ ጌታ በታላቅ ምልክቶች እና ተአምራት ራሱን ይገልጥላቸው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 8ን ተመልከቱ) ። ፊሊጶስም በሰማሪያውያን መካከል በሚያገለግል ጊዜ፣እግዚአብሔር ወደ ምድረ በዳ ሄዶ አንድን ኢትዮጵያዊ ሰው ጋር እንዲነጋገር ተናገረው። የነበረውን ታዕምራዊ መነቃቃትን በመተው በበረሃ ውስጥ አንድን ግለሰብ ለማገልገል ፊልጶስ ለእግዚአብሔር ጥሪ ታዛዥ ነበር።
ወደዚያ በረሃ ሄዶ ለማገልገል የእግዚአብሔር ጥሪ ቢደርሰኝ የምሰጠው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ብዙ ጊዜ አስባለሁ። በዚያ በሰማርያ ደቀ መዛሙር መሆን እና የእግዚአብሔርን ቃል መማር የሚያስፈልጋቸው አዲስ የመጡ ሰዎች ነበሩ። በእርግጥ ይህ አስፈላጊ ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለፊሊጶስ ለሕይወቱ ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር አሳየው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ሁልጊዜ ከእኛ ጋር አንድ አይደሉምና።
ጌታን በምታገለግሉበት ጊዜ እግዚአብሔር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር አብሮ ከመሄድ ይልቅ ሰዎችን ለማስደሰት እና የእነሱን ይሁንታ ለማግኘት እንፈተን ይሆናል። እግዚአብሔር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ጋር በሚስማማ መልኩ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወታችሁን እና አገልግሎታችሁን በቁጥሮች እና በስታትስቲክስ ለመለካት ትፈተኑ ይሆናል። ከእግዚአብሔር ጋር የምታደርጉትን ጉዞ እንዲሁም ቅዱስ ልብ እና አዕምሮን ከማሳደግ ችላ እንድትሉ ፈተና ሊገጥማችሁ ይችላል። ስኬታማ መሆን ይቻላል፤ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር እና እርሱ ለህይወታችን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የማይስማማ ሊሆን ይችላል።
እዚህ ልንረዳው የሚያስፈልገን ጉዳይ እግዚአብሔር መንግስቱን ለማስፋት እኛን ሊጠቀምበት ይፈልጋል። ዳሩ ግን እርሱ ለእኛ ያዘጋጀው ዓላማ ይህ ብቻ ልናስተውል ይገባል። እኛ እግዚአብሔር በእጆቹ ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች በላይ ነን። እንግዲህ ከእርሱ ጋር ወዳለው ሕብረት ተጠርተናል። ይህ ማለት እርሱ በእኛ አንድ ሥራ መሥራት ይፈልጋል ማለት ነው። ሊመራን እና ወደ ዓላማዎቹ ሊወስደን ይፈልጋል። መንገዶቹ ብዙውን ጊዜ ከእኛ የተለዩ ናቸው። እሱ “ስኬታማ” ከሚመስል አገልግሎት በጣም ጸጥ ወዳለ ነገር ሊወስደን ይችላል። እንደፈለግን ማገልገል በማንችልበት እና በሕመም ምክንያት በአልጋ ላይ ራሳችንን የምናገኝበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። በእነዚህ ጊዜያት እግዚአብሔር አይተወንም። ለህይወታችን ያለውን የእርሱን ዓላማ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በተሻለ ለመለየት የምንችለው በእነዚህ የምድረ በዳ ጊዜያት ውስጥ ነው። ዓለማዊ ስኬት ሁልጊዜ እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። ዓለማዊ ስኬትን ግባችን ካደረግን፣እግዚአብሔር ለሕይወታችን ካለው ዓላማ ጋር ልንተላለፍ እንችላለን።
ለምልከታ፡
• በሕይወታችን እግዚአብሔር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች መኖር ባንችል ፍሬያማ መሆን እንችላለን?
• በሕይወታችሁ እና አገልግሎታችሁ እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች አላችሁን?
• ፍሬያማ መሆን ወይም በአገልግሎት ውስጥ እግዚአብሔር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች መመላለስ የበለጠ አስፈላጊ ነውን?
• ለሕይወታችንና ለአገልግሎታችን የእግዚአብሔርን ቅድሚያዎች በመግለጥ ረገድ ቅዱሳት መጻሕፍት ምን ሚና አላቸው? የእግዚአብሔር ቃል ተማሪ ናችሁን?
ለጸሎት፡
• በሕይወታችሁ እግዚአብሔር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች መመላለስ ትችሉ ዘንድ ጌታ እንዲረዳችሁ ጸልዩ።
• ሕይወታችሁን በትምህርቱ እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ጋር ታስተካክሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት እና ጸጋን ለመካፈል ጊዜ መስጠት እንድትችሉ ጌታ እንዲረዳችሁ ጸልዩ።
• ሁልጊዜ እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች በእኛ ዘንድ ባይሩም እንኳን እርሱ አሁንም ለክብሩ ሊጠቀምብን ስለሚችል ጌታን አመስግኑት።
ምዕራፍ 12 - በድካም ውስጥ ያለ ፍሬያማነት
በዚህ ጥናት ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር ዓላማውን ለማሳካት ጥንካሬያችንን በመጠቀም እንደማይወሰን ተመልክተናል። መንግሥቱን በዚህ ምድር ላይ ለማራመድ የሰዎችን ድክመቶች እና ውድቀቶች ይጠቀማል።
እግዚአብሔር ድክመቶቻችን እና ውድቀቶቻችን ለክብሩ ሊጠቀምባቸው ይችላል። የፈርዖን አመጸኝነት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከባርነት ነጻ ለማውጣት እና አስደናቂ የሆነውን የእግዚአብሔርን ኃይል ለመግለጥ አይነተኛ መሳሪያ ነበር። የዳዊት ወንጭፍ ከግዙፉ ጎልያድ ሰይፍና ጦር ጋር ሲወዳደር ምንም አልነበረም፤ነገር ግን ፍልስጤማውያንን ሁሉ ድል የተነሱት በዚያ ወንጭፍ ነበር። ክብሩ ወደ እግዚአብሔር እንጂ ወደ ሙሴ እንዳይሄድ እግዚአብሔር ሙሴን እስኪያረጅ ድረስ ጠበቀው። የፈረሰው የሆሴዕ ጋብቻ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ጸጋና ትዕግሥት የሚያስተምር ኃይለኛ ምሳሌ ነው።
እግዚአብሔር የእኛ ጥንካሬ አያስፈልገውም– እሱ የእኛን ድክመቶች እና ውድቀቶች እንዲሁ ሊጠቀም ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የተናገረውን አድምጡ፡
26 ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም።27 ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤28 እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥29 ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። 30-31 ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። (1ኛ ቆሮንቶስ 1)
ሐዋርያው የሚናገረውን አስተዋላችሁን? እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መምረጡን ጳውሎስ ያስታውሰናል። ብርቱዎችን ሊያሳፍር ደካሞችን ተጠቀመ። እግዚአብሔር ዓላማውን ለማሳካት የእኛን ታላቅ የሆነ ጥበብ እና ተሞክሮ አያስፈልገውም። ኩራታችን በጌታ እና እርሱ በሚሰራው ብቻ ነውና።
እግዚአብሔር ደካማ ነገራችንን የሚጠቀምበት ይህ ሃሳብ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚያስደስተው ይመስል ነበር። እንደገና ለቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ሲጽፍ እንዲህ ይል ነበር፡
6 ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።7 ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። 8 ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 9 እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 10 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።
በዚህ ምንባብ ውስጥ በጣም ጠንካራ የሆኑ ግንዛቤዎች አሉ። ጳውሎስ የሥጋ መውጊያ እንደ ተሰጠው ይናገራል። ስለዚህ ከእርሱ እንዲወሰድ ጌታን በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚያ መውጊያ ጋር እንደሚኖር ተናገረው። ይህ የሆነበት ምክንያት የእግዚአብሔር ኃይል በጳውሎስ ድክመት ፍጹም መሆን ስለነበረበት ነው። ጳውሎስ በሥጋ መውጊያው ምክንያት የተፈጠረውን ይህን ድክመት በመቀበል እግዚአብሔር ይህንን ደካማነት ተጠቅሞ ዓላማውን ለመፈጸም በመቻሉ ይደነቅ ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች “እኔ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” (2ኛ ቆሮንቶስ 12:6) ይላቸው ነበር።
እግዚአብሔር የእኛን ጥንካሬ እንደማይፈልግ ማወቁ እንዴት አይነት ትህትና ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ብዙጊዜ የእኛ ጥንካሬ እና ተሞክሮ እንቅፋት ሲሆን ይስተዋላል።አይኖቻችንን ከእግዚአብሔር ላይ አንስተው በራሳችን ላይ እንድናደርጋቸው ምክንያት ይሆናል። በጌታ እና በመንፈሱ ሥራ ላይ ሳይሆን በራሳችን ችሎታ መታመን እንጀምራለን።
ይህ ማለት እግዚአብሔር ጥንካሬአችንን መጠቀም አይችልም ማለት አይደለም። ለመንግስቱ እንጠቀምበት ዘንድ የሚጠብቀንን መንፈሳዊ ስጦታዎች ይሰጠናል። በአገልግሎቱ የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን የሚቀርጹንን እና የሚያሳድጉንን ልምዶችን ይሰጠናል። ሆኖም እግዚአብሔር ሥራውን በሰው ብርታት ምክንያት እንደሚገድብ አታስቡ። በዚህ ጥናት ውስጥ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ በዓላማ ያመፁ ሰዎችን ሲጠቀም ተመልክተናል። እግዚአብሔርን የማያውቁ ሌሎችንም ደግሞ ተጠቅሟል። እግዚአብሔር የጳውሎስን ድክመት እና ጥንካሬዎች ተጠቅሞበታል።
ከራሳችን “እግዚአብሔር የሚጠቀምብኝ ለዚህ ነው” የምንለውን ነገር ለማግኘት የምንፈልግ ሰዎች ምንኛ ምስኪኖች ነን? ከብርታታችን የተነሳ እግዚአብሔር እየተጠቀመብን እንደሆነ እንዲሰማን እንፈልጋለን፣ነገር ግን ጳውሎስን ወይም ሙሴን በድካማቸው ሲጠቀም እናያለን። እሱን በጣም በመቅረባችን ምክንያት እኛን እንደሚጠቀምብን ማመን እንፈልጋለን ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚቃወመውን እና ከእሱ የሚሸሸውን ዮናስን ወይም እግዚአብሔርን እንኳን የማያውቀውን ቂሮስን እንዴት እንደተጠቀመበት አንብቡ። እኛ እግዚአብሔር የተጠቀመብን ፈቃደኞች ስለሆንን እንደሆነ ማመን እንፈልጋለን፣ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ሕብረት ስለሌለው ነገር ግን ተዕምራቶቹን ለእስራኤል እና ለግብፅ ሕዝብ ለመግለጥ ስለተጠቀመበት ስለ ፈርዖን ተምረናል።
እግዚአብሔር የተጠቀመባቸውን ወንዶች እና ሴቶች ታሪኮችን ስናነብ፣አንዳንድ ጊዜ በጣም በመጥፎ ሁኔታ እንመለከታቸዋለን። አመፃቸውን፣ድክመታቸውን እና የእግዚአብሔርን ዓላማ ውድቅ ሲያደርጉ እንመለከታለን። ከመካከላቸው በጣም ጥሩው የሆነው እንኳን ፍጹም አይደለም። እግዚአብሔር በዚህ ምድር ላይ የእርሱን ዓላማዎች ለማሳካት ደካማ ወንዶችን እና ሴቶችን ይጠቀማል። መንግሥቱን ለማራመድ የእነዚህን ወንዶችና ሴቶች ደካማ ነገሮች ይጠቀማል። እሱ የሰዎችን አመፅ በመጠቀም ለስሙ ምስጋና ያመጣል፡
10 ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ። (መዝሙር 76)
ዮሴፍ በተቆጡ ወንድሞቹ ለባርነት ተሽጦ ነበር፣ነገር ግን እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ መዳን ለመፈጸም የወንድሞቹን ንዴት ተጠቅሟል። በዮሴፍ በኩል መላው የእስራኤል ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከሚያጠፋቸው ታላቅ ረሃብ ድነዋል (ዘፍጥረት 37፡26-28 ተመልከቱ) ።
ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎን ጣዖት ለማምለክ እና ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ንጉሥ ናቡከደነፆር እጅግ ተቆጣ። በዚህም ምክንያት ወደ እቶን እሳት ወረወራቸው። በዚያም የጌታ መልአክ ለሦስቱም ከመቃጠል ጠበቃቸው። ናቡከደነፆርም ይህን አይቶ የሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎን አምላክ አመለከ (ዳንኤል 3ን ተመልከቱ) ።
ሌላው ምሳሌ በክርስቶስ ስቅለት ጌታ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ቁጣ ለስሙ ውዳሴ ለማምጣት የተጠቀመበት መንገድ ነው። ጌታ ኢየሱስን ውደ መስቀል ሞት የወሰደው የዚያን ዘመን ሰዎች የቅናት ቁጣ ነበር። እግዚአብሔር ሞቱን ተጠቅሞ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ድነትን እንዲሁም ለስሙ ታላቅ ውዳሴን አመጣ።
እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ቁጣ ተጠቅሞ መንግስቱን ሲያራምድ ስናይ በጥንካሬዎቻችን መመካት እንችላለን? በእኔ ጥንካሬ እና ዝግጁነት ብቻ እግዚአብሔር እንደሚገድብ በግልጽ ማመን እችላለሁን? እሱ ከዚህ አይበልጥምን? የዚህ ዓለም ዕጣ ፈንታ በእኔ እጅ አይደለምና። እርሱ በእኔ መቻል እና አለመቻል የሚገደብ አምላክ አይደለም። የእግዚአብሔር ሥራ በሰው ልጅ ክፋት የሚሰናከል በሰይጣንም የሚሸነፍ አይደለምና።
ታላቁ ፈጣሪ እግዚአብሔር ዓላማዎቹን እየፈጸመ ነው። ድክመቶቻችን እና ውድቀቶቻችን ቢኖሩም እነዚያ ዓላማዎች እየተፈጸሙ ናቸው። የሰው ልጅ ቁጣ ዓላማዎቹን አያደናቅፍም። እርሱ ከድክመታችንን ሁሉ ይበልጣልና። የእኛን ድክመቶች እንኳን ተጠቅሞ የእርሱን ዓላማዎች ለማስፈጸም ይጠቀማል። በዚህ ውስጥ ታላቅ ተስፋን ማግኘት እንችላለን።
ለምልከታ፡
• እግዚአብሔር ክብርን ለራሱ ለማምጣት የአገልጋዮቹን ድክመቶች እንዴት እንደተጠቀመ አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጡ?
• በጌታ አገልግሎት ውስጥ ጥንካሬያችን እንቅፋት የሚሆንብን እንዴት ነው?
• በፍሬያማነታችን መኩራራት ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? ክብር ሁሉ የተገባውስ ማን ነው?
• እግዚአብሔር ለስሙ ውዳሴን ለማምጣት የሰዎችን ቁጣ እንዴት ይጠቀማል?
ለጸሎት፡
• ድካማችንን እንኳን ለክብሩ እና ለመንግሥቱ መስፋፋት ሊጠቀምበት ስለሚችል ጌታን አመስግኑ።
• ጌታ በህይወታችሁ ላደረገው ነገር ክብርን ለመውሰድ የፈለጋችሁበትን ጊዜዎች ይቅር እንዲላችሁ ጸልዩ።
• እርሱ ከኃጢአተኞች ቁጣ እንኳን የሚበልጥ መሆኑን እና ለቅዱስ ስሙ ውዳሴን ለማምጣት ቁጣቸውን ስለሚጠቀም ጌታን አመስግኑት።
ምዕራፍ 13 - የማጠቃለያ ሐሳቦች
በዚህ ጥናት ውስጥ እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸውን ዓይነት ሰዎች ተመልክተናል። ከእነዚህ ምሳሌዎች የመጡ አንዳንድ እውነታዎችንም መርምረናል። በዚህ የመጨረሻ ምዕራፍ የተመለከትናቸውን ስለ እውነት የቀረቡ አንዳንድ ቁልፍ መርሆችን እና አተገባበሮችን ማጠቃለል እፈልጋለሁ።
ፍሬያማነት በዋነኝነት የተመሠረተው በእኔ ብርታት ወይም ዝግጁነት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ነው
በዳሰስናቸው ምሳሌዎች ውስጥ እግዚአብሔር ለሥራው ደካማ ወይም ዓመፀኛ የሆኑ ወንዶችን እና ሴቶችን እንዴት እንደተጠቀመ ተመልክተናል። እግዚአብሔር ብርታቴን እና ልምዴን ሊጠቀም ይችላል ሆኖም እርሱ እኔን ለማስተማር እና መንግስቱን ወደፊት ለማራመድ ድክመቴን እና ውድቀቴን ሊጠቀም ደግሞ ይችላል። ጌታ እንዲጠቀምባቸው ዝግጁ የሆኑትን ወይም እስከመጨረሻው እርሱን የሚቃወሙትን ሲጠቀም ተመልክተናል። እግዚአብሔር በሚወስነው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲጠቀምባቸው ዝግጁ የሆኑትን በማንኛውም ጊዜ ሊጠቀም ይችላል። እሱ በእኛ ጥንካሬ እና ዝግጁነት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ዓላማዎቹ ከእኛ ወይም ከድካማችን ያለፈ ነውና፡፡
ፍሬ ማፍራት የምችለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። በዋናነት እኔ ጥሩ ወይም ጠንካራ ስለሆንኩ ሳይሆን እግዚአብሔር እኔን ለመጠቀም ስለመረጠ ነው። ይህ ማንኛውንም ኩራት ያስወግዳል። የምመካው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው። ፍሬ የሚፈራው ፍጽምና በሌለው ሰው በሚሆን የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው። ያለ እርሱ በመንግሥቱ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ፍሬ ማፍራት አልችልም። በድካሜ ብቻ ሳይሆን በብርታቴም በእርሱ ላይ እደገፋለሁ።
ፍሬያማነት ከእግዚአብሔር ጋር የምመላለስበት መለኪያ አይደለም
ሁለተኛው እዚህ ላይ ማንሳት ያለብኝ ጉዳይ በአገልግሎት ውስጥ ያለኝ ስኬት ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ የሕይወት ጉዞ መለኪያ አይደለም። ፍሬያማነትን ከታማኝነት መለየት አስፈላጊ ነው። ከእርሱ ጋር የተስማማ ሕይወት ባይኖረኝም እንኳን እግዚአብሔር ሊጠቀምብኝ ይችላል። በእውነቱ ከመካከላችን ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም በሆነ ሕይወት የሚመላላስ ማን አለ? እግዚአብሔር ፍጹም የሆኑትን ብቻ በመጠቀም አለመወሰኑ ምንኛ አመስጋኞች እንድንሆን ያግዘናል።
አገልግሎታቸው በዓለም ፊት ስኬታማ በሆነላቸው ሰዎች አትታለሉ። በአገልግሎቶቻቸው የተገኘው ስኬት ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ሕብረት እንደመጣ አድርጎ በማሳየት ብዙዎችን ያታለሉ ሰባኪዎች እና ወንጌላውያን አሉ። ሕይወታቸው ሲታይ ግን በጣም ብዙ ነገር ሊገልጥ ይችላል።
ስኬት ብለን በምንጠራው አንታለልም። ከዚያ ስኬት በስተጀርባ ካለው ሰው ውጭው ገጽታ ባሻገር መመልከት አለብን። ከጌታ ጋር በታማኝነት እየሄደ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እና በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት ሕይወቱን ለመምራት ይፈልጋልን?
“ስኬት” መጀመሪያ ቅድሚያ የምትሰጡት ጉዳይ አይሁን። ከጌታ እግዚአብሔር እና ከቃሉ ጋር በታማኝነት ለመጓዝ በፍጹም ልባችሁ ፈልጉ። ክርስቶስን ማወቅ እና ከእሱ ጋር መራመድ ከፍተኛ ግባችሁ ይሁን።
በታማኝነት እና በክርስቶስ መኖር ላይ ትኩረት አድርጉ
እንደ አማኝ፤ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን እና በእርሱ በመኖር ላይ ትኩረት ስለማድረግ መማር አለብን። ኤርምያስ ለአርባ ዓመታት በዘለቀው አገልግሎቱ ለድካሙ እንዲሆን ያየው ፍሬ ትንሽ ነበር። በእርግጥ እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው እግዚአብሔርን ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ይሰብክ ዘንድ ነው፡
27 በዚህም ቃል ሁሉ ትነግራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ትጠራቸውማለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም። (ኤርምያስ 7)
ከሰው እይታ አንጻር፣አገልግሎቱ የተሳካ አልነበረም፣ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ፊት ታማኝ ነቢይ ነበር። ኤርምያስ በአገልግሎቱ መጨረሻ ላይ ለዓመታት ስብከቱ ያሳየው እንብዛም ነበር ይሁን እንጂ እርሱ ታማኝ ስለነበር ሽልማቱን በእርግጥ ይቀበላል።
በአገልግሎታችሁ አነስተኛ ፍሬን ብታዩ እንኳን በሥፍራችሁ ላይ ትቆማላችሁን? የምትፈልጉትን ምላሽ ባታገኙ እንኳን መስበካችሁን ትቀጥላላችሁን? ለበለጠ ፍሬያማ አገልግሎት ሲሉ ብዙዎች በእግዚአብሔር የተመደቡበትን ሥፍራ ትተው ሄደዋል። በትናንሽ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የኖሩት የት ይገኛሉ? በእግዚአብሔር እውነት ወደ ሩቅ ገጠራማ ስፍራዎች እየተጓዙ የሚያገለግሉ ዛሬ ያሉት ነው? ለታማኝ ጥረታቸው ምንም ባያዩም እንኳን የጸኑት የት አሉ? እውነተኛ ስኬት የሚለካው በቁጥራዊ ስሌት እና በስታትስቲክስ ሳይሆን በታማኝነት እና በመታዘዝ ነው።
በዘመናችን ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉት ታላላቅ ችግሮች አንዱ ከቁጥራዊ ስሌት ውጪ ከሆናችሁ ትልቅ ድክመት እና መንፈሳዊ አለመብሰልን ልታገኙ ትችላላችሁ። አዎን፣በርካታ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ይመጣሉ ዳሩ ግን የእነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት ነው? ፍሬያማ ልንሆን እንችላለን፣ነገር ግን በትንሽ ነገሮች እንኳን ታማኝ ነን? ወደ እግዚአብሔር ቀርበን እርሱን እየተለማመድን ነውን? እግዚአብሔር ከቁጥራዊ ስሌቶች ባሻገር ወደ ግለሰቦች የልብ ጥራት ይመለከታልና።
ታዛዥ ሁኑ እግዚአብሔርም እንደፍቃዱ እንዲጠቀምባችሁ ፍቀዱ
የእያንዳንዳችን ፈተና ለእግዚአብሔር እና ለቃሉ በመታዘዝ መመላለስ ነው። የእርሱ ሃሳብ በእኛ ሊፈጸም የሚችለው በእሱ ስንኖር እና ለቃሉ ታማኝ ስንሆን ብቻ ነው። ለእርሱ ከምንሠራው ይልቅ እግዚአብሔር ስለ እኛ በጣም እንደሚያስብ አምናለሁ። ይህን ካልኩ በኋላ ግን፣ ከእርሱ ጋር በታማኝነት ስትሄዱ እግዚአብሔር እንደሚጠቀምባችሁ እርግጠኛ ሁኑ።
ኢየሱስ በዮሐንስ 15 ይህን የተስፋ ቃል ሰጥቷል፡
5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። (ዮሐንስ 15)
እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፡
8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። (ዮሐንስ 15)
እግዚአብሔር የመንግሥቱን ሥራ ለማስፋፋት ሊጠቀምብን ይፈልጋል። ሆኖም እርሱ እንድናገለግለው የሚፈልገው በእርሱ ስንኖር ብቻ እንደሆነ አስተውሉ። በእርሱ መኖር ማለት ምን ማለት ነው? ከእርሱ ጋር በማያቋርጥ ሕብረት እና አንድነት ውስጥ መኖር ማለት ነው። ለእርሱ እና በሕይወታችን ላለው ዓላማ ራሳችንን አሳልፎ መስጠት ነው። በእኛ እንደወደደ ይሰራ ዘንድ መፍቀድ ነው። እኛ የእርሱ መሣሪያዎች ነንና። በክርስቶስ የሚኖር የገዛ ዕቅዶቹ እግዚአብሔር ካዘጋጀው እቅድ ጋር እንዲጋጭ የማይፈቅድ ነው። በእርሱ መኖር ማለት በሕይወታችን ለእግዚአብሔር እና ለእርሱ ሃሳቦች መገዛት ነው። በምናደርገው እና በምንሰራው ሁሉ ላይ ሙሉ ቁጥጥር መስጠት ነው። በእርሱ መኖር ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅ ቅርበት ባለው ሥፍራ መቆየት ነው።
የወይኑ ቅርንጫፍ ሙሉ በሙሉ የተደገፈው በወይኑ ግንድ ላይ ነው። የወይኑ ግንድ ኃይል በዚያ ቅርንጫፍ ውስጥ ስለሚፈስ ፍሬ እንዲያፈራ ያደርገዋል። በክርስትና ሕይወታችን የሚሰራው እንዲህ ነው። በክርስቶስ ስንኖር እና ለእርሱ ስንገዛ፣በውጤቱ የክርስቶስ ሕይወት በእኛ ውስጥ ይፈሳል። የክርስቶስ ሕይወት በእኛ ውስጥ ሲፈስ በእኛ የሚፈራው የመንፈሱ ፍሬ ይሆናል። የወይኑን ባህርይ መውሰድ እንጀምራለን። የወይኑን ባህርይ ስንካፈል፣በዚህ ዓለም ጨለማ ውስጥ ብርሃናችን እና ምሳሌያችን ያበራል። ሰዎች ያንን ብርሃን እና መልካም ሥራዎቻችንን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችንን ያከብራሉ (ማቴዎስ 5:16ን ተመልከቱ) ።
እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ሊሠራው ስለሚፈልገው ስለ እነዚህ መልካም ሥራዎች መረዳት ያለብን፤በሕይወታችን ውስጥ የሚሠራው የመንፈሱ ፍሬ እንጂ የሰው ጥረት ውጤት አለመሆኑን ነው። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ሊያፈራው የሚፈልገው ፍሬ በእርሱ የመኖራችን ውጤት ነው። የዚህ ፍሬ ምንጭ እሱ ነውና።
በአገልግሎት እያደግሁ ስመጣ ጌታ ከሚያሳየኝ አንዱ ነገር በሰው ፍሬ እና ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚመጣው ፍሬ መካከል ልዩነት መኖሩን ነው። እግዚአብሔርን የሚያገለገሉ በርካታ ሰዎች አሉ። እኔ የምፈልገው ግን እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት እንዲሰራ ነው። ከምድራዊ ጥበቤ እና ተሞክሮዬ ይልቅ የጌታን መሪነት ባመንኩበት ቦታ የበለጠ መሆን እፈልጋለሁ።
ጌታ መጽሐፍትን በመጻፍ እና በማሰራጨት ረገድ የሰጠኝን አገልግሎት ስመለከት፣ እግዚአብሔር በሚያደርገው ነገር ብዙጊዜ እደነቃለሁ። ይህንን አገልግሎት ለማስቀጠል የሚያግዙ ሃብቶች ከየት እንደመጡ ስመለከት ብዙ ጊዜ እገረማለሁ - በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት ይሰራጩ ዘንድ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ባርኮናል። መጽሐፍትን ስለማገኘት ጥያቄዎችን ከሚያቀርቡ በርካታ የማላውቃቸው ሰዎች ኢሜይሎችን እና ደብዳቤዎችን እቀበላለሁ። እኔ ብዙ ጊዜ እነዚህ ሰዎች አድራሻዬን እንዴት እንዳገኙ አስባለሁ - በእርግጥ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። መጽሐፉ ለመባረክ ወይም መጋቢዎችን እና ሌሎች አገልጋዮችን በእግዚአብሔር እውቅት ለማስታጠቅ በትክክለኛው ጊዜ እንዴት እንደደረሰ የሚነግሩኝ ደብዳቤዎች ይደርሱኛል– የእግዚአብሔር ጊዜ ፍጹም ነው። እነዚህ ሁሉ እኔ ያቀድኳቸው ነገሮች አይደሉም። እግዚአብሔር ይህንን አገልግሎት ሲመራ ቆይቷል ፣ እኔ ማድረግ የምችለው በመከተል እና በመታዘዝ መውጣት ብቻ ነው።
በተወሰነ አቅጣጫ በራሴ እውቀት እና ጥበብ ለመራመድ የፈለግኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ይህን ለማድረግ ብሞክርም፣ ስጸልይ እና በምትኩ የእግዚአብሔርን እርዳታ ስጠብቅ ራሴን አገኛለሁ። እግዚአብሔር ደግሞ ጸሎቴን ይሰማል። እሱ ጊዜው ሲደርስ ትክክለኛ የሆኑ ሰዎችን እና ሃብቶችን ይሰጣል። እኔ የዚህ አገልግሎት ዳይሬክተር አይደለሁም። እኔ ለሰማያዊው ዳይሬክተሬ ታዛዥ ለመሆን የምፈልግ አገልጋይ ብቻ ነኝ። እንዲሆንልኝ የምፈልገው በዚህ መንገድ ነውና። የዚህ አገልግሎት ፍሬ እና አቅርቦት ከእግዚአብሔር እንጂ የሰው ጥረት ውጤት እንዲሆን አልፈልግም። በክርስቶስ የሚኖር ሕይወት ፍሬ እንዲሆን እመኛለሁ።
የፍሬያማነት በረከት
ለጌታ በመታዘዝ እና በመገዛት የሚመጣ ፍሬያማነት አለ። ይህ ፍሬ ለእግዚአብሔር እና ለመንገዶቹ እጅ ከመስጠት የሚመጣ ውጤት ነው። መታዘዝን የሚጠይቅ ቢሆንም የሰው ጥረት ውጤት አይደለም። የወይኑ አካል መሆን ተፈጥሯዊ ውጤት ነው። ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ውጤት ነው።
የዚህ ፍሬያማነት በረከት እግዚአብሔር በእኛ እየሠራ የመሆኑ እውነታ ነው። የክርስቶስ ሕይወት በእኛ የመፍሰሱ ማስረጃ ነው። በዳንኤል 4፡30 ላይ እንደ ናቡከደነፆር መንግስታችንን መመልከት እንችላለን፡
30 ንጉሡም፦ ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ። (ዳንኤል 4)
በሰው ጥበብ እና ጥንካሬ ብዙ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። በርካታ ትልልቅ የንግድ ሥራዎች እና በዓለም ላይ ያሉ ሐገሮች በሰው ጥበብ እና ጥንካሬ ተገንብተው ተንቀሳቅሰዋል። ሕይወታችሁን እና አገልግሎታችሁን ስትመለከቱ እና “ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን የሠራሁትን ተመልከቱ” ስትሉ አስተውሉ። ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ “ጌታ ያደረገውን እዩ” ማለቱ ምን ያህል ድንቅ ይሆን? እግዚአብሔር ያደረገውን ስመለከት ልቤ በምስጋና እና በመደነቅ ይሞላል። የእርሱን መገኘት እና ጸጋ ውጤት እመለከታለሁ። እሱ እኔን እንደ ዕቃ አድርጎ ሊጠቀምብኝ እንደሆነ ሳስብ እደነቃለሁ። ብርታቱን እና ጸጋውን በእኔ ለመግለጽ በመምረጡ በጣም ተደስቻለሁ። ይህ ሁሉ ትሁት እና በእግዚአብሔር እና በአዳኜ ፊት ተንበርክኬ እንድሰግድ ያደርገኛል።
የዚህ ዓይነቱ ፍሬያማነት በረከት በእግዚአብሔር እና በክብሩ ፊት እንጂ በፍሬው ውስጥ አይደለምና። ብዙውን ጊዜ ያንን ፍሬውን ወይም መሣሪያ የሆነውን ሰው እናመልካለን። እውነተኛው ክብር የዚያ ፍሬ ምንጭ የሆነው ጌታ እግዚአብሔር ራሱ ነው። ጌታ ክብሩን ሲቀበል ማየት የአማኙ ታላቅ ደስታ ነው። የእግዚአብሔርን መገኘት እና ኃይሉን ማወቅ የአማኙ ታላቅ ደስታ ነው።
የእግዚአብሔር ኃይል በእኛ ውስጥ ሲፈስ ማየት እንዴት ይገርማል።የእኛ ብርታት ሳይሆን የእርሱ መሆኑን እናውቃለን። የሚያበረታን የሚያስታጥቀን እርሱ መሆኑን እናስተውላለን። የእርሱን መኖር እና በእኛ ውስጥ የሚፈስውን የወይኑን ሕይወት እናውቃለን። በዚህም ደስ ይለናል ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው ለዚህ ነው።
ለምልከታ፡
• ስኬት ለእናንተ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ዓለም ስኬትን እንዴት ይገልጻል? ይህ እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነውን?
• በክርስቶስ መኖር ማለት ምን ማለት ነው?
• ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ማድረግ እና እግዚአብሔር በእኛ አንድ ነገር ሲያደርግ መካከል ያለው ልዩነት ምንድ ነው?
• የአገልግሎታችን እና የኑሮአችን መሪ በመሆን የእግዚአብሔርን ቦታ መውሰድ ይቻለን ይሆን?
• “ያደረግሁትን ተመልከቱ” እና “እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከቱ” በሚሉት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?
• በሕይወታችሁ እና በአገልግሎታችሁ ያለው የእግዚአብሔር ማስረጃ ምንድ ነው?
ለጸሎት:
• ለሕይወታችሁ እና አገልግሎታችሁ እርሱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ይኖራችሁ ዘንድ ጌታ እንዲረዳችሁ ጸልዩ፡፡
• ለእሱ እና ለዓላማው በበለጠ ሙሉ በሙሉ ትገዙ ዘንድ እንዲረዳችሁ እግዚአብሔርን ይጠይቁ።
• ኃይሉን እና ጥበቡን በእኛ ውስጥ ማፍሰስ ስለሚወድ ጌታን አመስግኑት። እኛን ለክብሩ እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ፈቃደኛ ስለ ሆነ አመስግኑት።
• በእናንተ በሚያደርገው እና ለእሱ ልታደርጉለት በሚፈልጉት መካከል ያለውን ልዩነት ማየት ትችሉ ዘንድ እንዲረዳችሁ እግዚአብሔርን ጠይቁ።
ላይት ቱ ማይ ፓዝ የመጽሐፍ ስርጭት
ላይት ቱ ማይ ፓዝ (LTMP) በእስያ፤በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ የሚገኙ ድሃ ክርስቲያን አገልጋዮችን የሚደርስ የመጽሐፍ ስርጭት አገልግሎት ነው። በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያን አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጠና ለማግኘት ወይም ለአገልግሎቶቻቸው እና በግል ለመታነጽ የሚሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቁሳቁሶችን ለመግዛት አስፈላጊ የሆኑ ሃብቶች የሏቸውም።
ኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌኦድ የአክሽን ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪስ አባል ሲሆን በዓለም ዙሪያ ላሉ ድሃ ክርስቲያን አገልጋዮች ይሰራጩ ዘንድ ዓላማን በማንገብ እነዚህን መጽሐፍቶች ሲጽፍ ቆይቷል።
እስከዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ መጽሐፍት ከስድሳ በላይ በሆኑ አገራት ውስጥ ለስብከት፤ለማስተማር፤ለወንጌል ስርጭት አገልግሎት እና ለአከባቢው አማኞች ማበረታቻ ጥቅም ላይ ውለዋል። አሁን መጽሐፍቶቹ ወደ በርካታ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ዓላማው በተቻለ መጥን ለሁሉም አማኞች ተደራሽ ማድረግ ነው።
የ(LTMP) አገልግሎት በእምነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ነው፤በዓለም ዙሪያ ያሉ አማኞችን ለማበረታታት እና ለማነጽ መጽሐፍቶቹ ይሰራጩ ዘንድ ለእነዚህ አስፈላጊ ሃብቶች ጌታን እንታመናለን። ጌታ እነዚህን መጽሐፍት ለመተርጎም እና የበለጠ ለማሰራጨት በሮችን ይከፍት ዘንድ በጸሎት ታግዙናላችሁን? ስለ ላይት ቱ ማይ ፓዝ የመጽሐፍ ስርጭት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ www.lighttomypath.ca